የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

50
ፌስቡክ ትሩፋት በፍቃዱ ኃይሉ ፳፻፭

description

የፌስቡክ ትሩፋት - በፌስቡክ በኩል ለወዳጆቼ ያጋራሁዋቸውን ግጥሞች ሰብስቤ ያቀናበርኩት መድብል ነው::

Transcript of የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

Page 1: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ፳፻፭

Page 2: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

© በፍቃዱ ኃይሉ 2005

Page 3: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

ማውጫ 1. ??? ------------------------------------------------------------------------------------ 1 2. እኔና... --------------------------------------------------------------------------------------------- 2 3. አንቺዬ --------------------------------------------------------------------------------------------- 2 4. አትፍረዱብኝ -------------------------------------------------------------------------------------- 3 5. Last of Lust ------------------------------------------------------------------------- 3 6. “የኛ ሰው” ----------------------------------------------------------------------------- 4 7. ነበር ቢሰበር --------------------------------------------------------------------------------------- 4 8. የአምባገነን ሥሪት --------------------------------------------------------------------------------- 7 9. ምልልስ ፩፡ የወር አበባዬ ------------------------------------------------------------------------- 9 10. ምልልስ ፪፡ የደራሲ ምኞት ---------------------------------------------------------------------- 11 11. ምልልስ ፫፡ ምክር ለሚሰሙ -------------------------------------------------------------------- 13 12. ምልልስ ፬፡ ምነው ሆዴ... ----------------------------------------------------------------------- 15 13. (ርዕስ አልባ)------------------------------------------------------------------------------------- 21 14. እምነት ሲለካ ----------------------------------------------------------------------------------- 22 15. ደሴ እና DC ------------------------------------------------------------------------- 22 16. ገዢና ተገዢ ------------------------------------------------------------------------------------ 25 17. ተገዢ እና ገዢ -------------------------------------------------------------------------------- 25 18. የምርጫ ቅስቀሳ -------------------------------------------------------------------------------- 26 19. የደም ውርስ ------------------------------------------------------------------------------------ 28 20. ከቃሌ እና ልቤ -------------------------------------------------------------------------------- 29 21. የአንድነት ቀኖና -------------------------------------------------------------------------------- 30 22. ፋኖሴ ------------------------------------------------------------------------------------------- 31 23. ለከንፈር ወዳጄ --------------------------------------------------------------------------------- 31 24. እስኪ ጽደቁብኝ ------------------------------------------------------------------------------- 32 25. R.I.P. ------------------------------------------------------------------------------ 33 26. መንገድ ---------------------------------------------------------------------------------------- 33 27. የጾም ጥብስ ----------------------------------------------------------------------------------- 34 28. ስልጣን እንዲቀና ----------------------------------------------------------------------------- 34 29. ትዝታ ዘ ሚያዚያ 30፤ 1997 ----------------------------------------------------------------- 35 30. ራስን ፍለጋ ----------------------------------------------------------------------------------- 36 31. ይደነግጣል ልቤ ------------------------------------------------------------------------------- 36 32. (ርዕስ አልባ) ---------------------------------------------------------------------------------- 37 33. ይብላኝ ላንቺ --------------------------------------------------------------------------------- 38 34. ከዚህና ከዚያ ---------------------------------------------------------------------------------- 39 35. ተዉ አትፍረዱበት ----------------------------------------------------------------------------- 41 36. ስለኔ ይወራል አሉ ----------------------------------------------------------------------------- 41 37. ያለውን የሰጠ --------------------------------------------------------------------------------- 42 38. ባይተዋርነት ----------------------------------------------------------------------------------- 42 39. በመጨረሻ... ---------------------------------------------------------------------------------- 43 40. ??? --------------------------------------------------------------------------------- 43

Page 4: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

አቤት ግጥም፣ ግጥም፣ ግጥም ደስ ማለቱ ገጣሚ በነበር ምናለ በቤቱ!

Page 5: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

መግቢያ

ሁሉም ቤት መግቢያ ያስፈልገዋል፤ አለበለዚያ ልቅ ሜዳ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ቤት

የሚመቱ ግጥሞች ስብስብ እንዲያው ነው፡፡ መግቢያ ያስፈልገዋል፡፡ በርግጥ መግቢያውን

ሁሉም ሰዎች እንዲያነቡት አይጠየቁም፡፡ ይህ መድብል እንዴት፣ በማን እና ለምን ተዘጋጀ

የሚል ጥያቄ ያላቸው ብቻ መልስ ይፈልጉበታል፡፡

ይህ የግጥም መድብል የተዘጋጀው፣ ባለፈው ዓመት (፳፻፬) በፌስቡክ ገጼ ላይ የለጠፍኳቸው

ግጥሞች ተሰባስቦ ነው፡፡ በርግጥ፣ ለአንዳንድ ግጥሞቼ፣ በፌስቡክ ጓደኞቼ የተሰጡኝን የግጥም

መልሶች ምልልስ ፩፣ ፪፣ ፫፣... እያልኩኝ አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ የሌሎች ገጣሚዎች

ቅምሻም አለበት ማለት ነው፡፡ እኔ ግጥም የምጽፈው ስለምችል ነው ማለት ድፍረት

ይሆንብኛል፤ ምክንያቱም የምጽፈው ስለምወድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ፤ ሰዎች

የሚሰጡት ምላሽ አበረታች ስለሆነም፣ እንደሐሳብም የሚያወያዩ ነገሮች አይጠፏቸውም ብዬ

በማሰብ በነፃ፣ ለሕዝበ በይነመረብ ተጠቃሚ እንዲደርስ ስል አዘጋጅቼዋለሁ፡፡

መቼም ‹‹ሰው የወለደውን ሲስሙለት፣ የደገሰውን ሲበሉለት ደስ ይለዋል፡፡›› ነውና ተረቱ፥

ግጥሞቼን ስታነቡልኝ የበኩር ደስታዬን አገኛለሁ፡፡ በ[email protected] በኩል

አስተያየታችሁን ስታደርሱኝ ደግሞ፥ በዚህ መስክ ቀጣይ ሥራዬ ምን መሆን እንዳለበት

እየገባኝ ይመጣል፡፡

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

ከምስጋና ጋር

Page 6: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

1

? ? ?

ሐያት በቁንጅና፣ ኃይሌ በEግሮቹ፣

ብርቱኳን በEስር፣ ቴዲ በግጥሞቹ፣

ሁሉም ቢወደዱ Eንደየስራቸው፣

ስለታመነ ነው Eንደሚ’ገባቸው፡፡

Eኔን ግን ያልገባኝ፥ ስኖር በዚች Aገር

ኑሮ የተወደደው ምን Aድርጎ ነበር?

(መስከረም 3፤ 2004)

የEናትን ቤት መሦብ የEንጀራ Eናት ወርሳው፣

Eንጀራው ቢኖርስ ማን ደፍሮ ሊቆርሰው?

(መስከረም 4፤ 2004 )

Page 7: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

2

Eኔና…

መኪናም ባይኖረኝ፥ በታክሲ Eሄዳለሁ፣

ቤትም ባልገነባ፥ ጎጆ Eከራያለሁ፣

የምዘንጥበት ገንዘብም ባይኖረኝ፣

ለጥቅም ያልሸጥኩት፥ ሕሊና ስላለኝ፣

ምቾት የማይገዛው፥ ልዩ ሰላም Aለኝ!!!

(መስከረም 16፤ 2004)

Aንቺዬ

ሳይሽ፣ ሳስብሽና ጊዜያችን ትዝ ሲለኝ፣

Eጅግ ብዙ ቢሆንም ስላንቺ የሚያስገርመኝ፣

ሳምንሽ ከመክዳትሽ ይልቅ የሚያስደንቀኝ ውዴ…

ፍቅር Eምቢ ቢልሽ’ንኳ፣ ይሉኝታ Aይዝሽም Eንዴ?!

(መስከረም 16፤ 2004)

Page 8: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

3

አትፍረዱብኝ

‹‹ትችላለህ፣ ትችላለህ፣ ትችላለህ›› ብላችሁኝ፣

ለመውረድ ከሚያስፈራበት ሽቅብ ሰቅላችሁኝ፣

እንዳልወርድ ፈርቼ እንጂ፥ መውረድ መች ጠላሁኝ?

(መስከረም 18፤ 2004)

Last of Lust

አንተ ትብስ፣ አንቺ - ተባብለን ሰኞ፣

ችላ ትይኝ ቃጣሽ - በአዳሩ ማክሰኞ፣

ረቡዕ ባሰብሽ - ታስቀይሚኝ ጀመር፣

ሐሙስ’ለት ታዘብኩሽ - በሰራሽው ነገር፣

ልቻላት በማለት - አርብ’ለት ባገኝሽ፣

ስልችት አደረግሽኝ - ቅዳሜ እንዳላይሽ፣

እንደምንም ብለሽ - ቅጠሪኝ እሁድ፣

ሳምንት’ንኳ ይሙላው - ፍቅራችን በግድ፡፡

(ሕዳር 2፤ 2004)

Page 9: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

4

“የኛ ሰው”

የሰው ስጋ በልተው፥ ከርሳቸውን የሚሞሉ፣

በሕዝቦቻቸው ስቃይ፥ የሚደሰቱት እያሉ፣

ያንተ መሰዋት የኔሰው፥ ቢያሰቅቅም ቅሉ፣

ከነሱ መኖር ይሻላል፥ መሞት ለወገን ሲታገሉ፡፡

(ሕዳር 6፤ 2003)

በዳውሮ ወረዳ ለታሰሩ ወጣቶች ፍትሕ እንዲሰጥ በማለት ሕዳር 1፤ 2003 ራሱን በእሳት

አጋይቶ ለሰዋው መምህር የኔሰው ገብሬ መታሰቢያነት፡፡

ነበር ቢሰበር

የኔና አንቺ ፍቅር፣ የኔና አንቺ ነገር፣

ቃላችን ባይበላው፣ ወድቆ ባይሰበር፤

እንኳን ሰዎች እና፣ ዓይተው የሚፈርዱት፣

እንኳን ወፎችና፣ መዘመር የሚያውቁት፣

እንኳን ዛፎችና፣ ሽብሻቦ የሚወዱት፣

ይቀኑበት ነበር፣ ጨረቃና ፀሃይ፣

ባሕር ውቅያኖሱ፣ ምድርና ሰማይ፡፡

ምን እነርሱ ብቻ፣ ቀንና ሌሊቱ፣

ውርጭና ሙቀቱ፣ በጋና ክረምቱ፣

በየብስም፣ በውሃም፣ በአየርም ያሉቱ፣

ሕይወት አለን ባዮች፣ የሞቱት ሳይቀሩ፣

በየመኖሪያቸው፣ በየመቃብሩ፣

ከኔና አንቺ በቀር፣ ሌላ እንዳያወሩ፣

ይመስሉ አልነበር ወይ በሕግ የታሰሩ?

- - -

የኔና አንቺ ፍቅር፣ የኔና አንቺ ነገር፣

Page 10: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

5

ቃላችን ባይበላው፣ ወድቆ ባይሰበር፤

በጠራራ ፀሃይ፣ ሕዝብ በሞላበት፣

በጠፉ ጨረቃ፣ እማኝ በሌለበት፣

ስንፋቀር ያዩ፣ የዓለም ፍጥረታት፣

ግዑዛን ክስተታት፣

እኛን መሆን ሽተው፣ ሌላ መሆን ጠልተው፣

የኔን ጥብቆና ያንቺን ቀሚስ ለብሰው፣

ወፎች ዘምረዋል፣ ዛፎች አርግደዋል፣

ውቅያኖሱ ሰክኗል፣ ሰማዩ ሰምይዋል፣

ውርጩ ለብ ብሏል፣ ሙቀቱ ቀዝቅዟል፣

ጨረቃና ፀሃይ አንድ ላይ ወጥተዋል፡፡

- - -

የኔና አንቺ ፍቅር፣ የኔና አንቺ ነገር፣

ቃላችን ባይበላው፣ ወድቆ ባይሰበር፤

ፈጣሪን ከሰማይ፣ ሰዉንም ከምድር፣

ከላይና ከታች፣ አስማምቷቸው ነበር፡፡

ጀማሪ አፍቃሪዎች፣ ኗሪ ተጋቢዎች፣

አግኝተው ያጡትም፣ ፍቅር ፈላጊዎች፣

ነገር ባርቆባቸው፣ ፍቅር የለም ባዮች፣

ወጣት ሽማግሌው፣ጥቁርና ነጩ፣

ሴትና ወንድ ሁሉ፣ ሁሉም በየፈርጁ፣

ምሳሌ ‘ሚያረጉት፣ በቃላት አጣፍጠው፣

እኔና አንቺን ነበር፣ ፊታቸው አስቀምጠው፡፡

- - -

ምን ዋጋ አለው ሆዴ፣ ቢጠራቀም ‹ነበር›፣

ወደጎን ቢለጠጥ፣ ሽቅብስ ቢከመር፣

ስለዚህ እንደዚህ፣ እስኪ እንመካከር፣

ሆድዬ….

Page 11: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

6

‹ነበር› ነበር እንጂ፣ መች ይሆናል ‹ነው›፣

ያፈረስነውን ቤት፣ ደግመን እንካበው፡፡

ይህንን የምልሽ ለኔ አስቤ አይደለም፣

ለአንቺም አላሰብኩም፣ የሚያስዋሸኝ የለም፣

ንቀን የተውነውን፣ ያን የድሮ ጎጆ፣

ናፍቄው አይደለም፣ ስሚኝ የኔ ቆንጆ፣

- - -

ይህንን የምልሽ ለኔ አስቤ አይደለም፣

ለአንቺም አላሰብኩም፣ የሚያስዋሸኝ የለም፣

ግና…

እስኪ እነዚያ ሁሉ፣ በእኛ የኮሩ፣

በፍቅራችን ዘመን፣ በምድር የኖሩ፣

‹ፍቅራቸው አያልቅም›፣ እያሉ ያወሩ፣

እንዴት በኛ ጥፋት፣ እነሱ ይፈሩ?

(ሕዳር 9፤ 2004)

Page 12: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

7

የአምባገነን ሥሪት

አባቴ…

አምሽቶ መግባቱ ሳያንስ፥ ድብን ብሎ ሰክሮ፣

ማጀቱን ከሳሎኑ ስታስማማ፥ የዋለችው እናቴን አስሮ፣

ሲደበድባት አይቻለሁ፣

ታዝቤው አልፌያለሁ፡፡

ያሻውን ሲያደርግ የሚያስፈቅደው፥ ራሱን ብቻ ቢሆንም፣

የኔና እናቴ ድርሻ ግን፥ ከሱ ታዛዥነት አያልፍም፡፡

ይህንንም አይቼ፣

አልፌዋለሁ ተከፍቼ፡፡

ቢሆንም…

ጀግና ማለት አባቴ፥ አባቴ ማለት ጀግና፣

ሁሉም ሰው በቤታችን፥ ይሸበርለታልና!

መምህሬ…

ትንሽ ጥፋት ሳጠፋ፥ አንበርክኮ ገርፎኛል፣

እግሬን በእጄ አጠላልፎ፥ ጆሮዬን አስይዞኛል፣

ቅጣቱን ተቀብያለሁ፣

የነገረኝን አምኛለሁ፡፡

ጠመኔውን እንደሲጃራ፥ በጣቶቹ መሃል ከትቶ፣

ሳት ብሎት ወዳፉ ሲሰድ፥ የገዛ ዓይኔ ተመልክቶ፣

አጫሽነቱን ገምቷል፣

ልቤ ተቀብሎታል፡፡

ቢሆንም…

መምህሬ ማለት አዋቂ፥ አዋቂ ማለት መምህሬ፣

ከኔ ይበልጣልና፥ በጉልበትም ሆነ በወሬ!

Page 13: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

8

አለቃዬ…

ሳረፍድና ስሳሳት፥ ደሞዜን ቆርጦ ቀጥቶኛል፣

በግምገማ ሰዓት፥ ሰነፍ ነው ብሎ ወንጅሎኛል፣

ሂሱን ተቀብያለሁ፣

ለመታረም ቃል ገብቻለሁ፡፡

ባስመዘገብኩት መልካም ውጤት፥ ሙገሳውን ተቀብሎ፣

እጆቹን ታጥቦ ሄዷል፥ ስህተቴን ለራሴ ጥሎ፣

ይህንንም አይቼ፣

ችዬዋለሁ ተከፍቼ፡፡

ቢሆንም…

አለቃዬ ማለት ትልቅ፥ ትልቅ ማለት አለቃዬ፣

ከላይ የመሆንን ጥቅም፥ መመልከቻ ምሳሌዬ፡፡

እኔ…

መሆን የምፈልገው፥ ስለነገ ባሰብኩ ቁጥር፣

ጀግና ልክ እንዳባቴ፣ ሞገሱ የሚያንጰረጵር፣

አዋቂ እንደመምሬ፣ ነገሩ የሚያመራምር፣

ትልቅ እንደአለቃዬ፣ ኃይሉ የማያጠራጥር፡፡

(ሕዳር 28፤ 2004)

Page 14: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

9

ምልልስ ፩

የወር አበባዬ

በወር አንዴ ብቻ ተናፍቆ እየመጣ፣

ለሦስት ቀናት ያህል እንደሎተሪ ዕጣ፣

አምበሽብሾ ‘ሚሄድ ሳያመሽ በጊዜ፣

የወር አበባ ነው ለኔ’ኮ ደሞዜ፡፡

(ሕዳር 29፤ 2004)

አንተስ ታድለሃል ደሞዝ ወር አበባህ፣

ሦስት ቀን ይቆያል፣

የእኔውስ ለጉድ ነው፣

ወዳጄ ይገርምሃል፣

ወዲያው እንደመጣ ትቶኝ እብስ የሚል፣

ነስር ሆኖብኛል፡፡

በፍቃዱ በየነ

Page 15: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

10

ላንዱ የወር አበባ፣ ላንዱ ነስር ሆኖ ላፍታ እያስቦረቀ፣

የኔው ለጉድ ሆኖ፣...

እንደ መስቀሉ ደም፣

ከምንጩ ሳይደርቅ፣ ለጥም እንደ ራቀ፣

ቆይ ነገ እንዳስባለ፣

እንደተጎመዠ፣ እንደ ተናፈቀ፣

ሲታለም ይቀራል፣

እዳ እየከፈለ፣ ያለፈ እየፋቀ፡፡

ዮሐንስ ሞላ

ብላችሁ ብላችሁ፣

በወር አበባዬ በደሜ መጣችሁ?

ሸፍኜ ያኖርኩትን ገሀድ ካወጣችሁ፣

እኔን ሳያርሰኝ ወዳ’ባይ መፍሰሱ ምነው ተረሳችሁ?

መሰረት ለማ

በብላሽም ቢሆን መልፋት መባተሉ፣

ተሁሉ፣ ተሁሉ ...

የደሞዝ ውጤቱ አሳቡ ነው ቃሉ፣

በልፋት የመጣ የዕለት ጉርስ ምንዳ፣

ደም - ወዝ መባሉ!

አንተነህ ተስፋዬ ለማ

Page 16: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

11

ምልልስ ፪

የደራሲ ምኞት

እባክህ ሐሳቤ በሐሳብ ተራቀቅ፣

የሆነች ልጅ ፍጠር ታሪኳ የሚደንቅ፣

የሆነም ልጅ ፍጠር በፍቅሯ የሚወድቅ፣

ችግር መሃላቸው ጎትተህ አስገባ፣

አንዳቸው ያልቅሱ አንባቢ እንዲባባ፣

ፍጠር፣ አኑራቸው፣ አመሰቃቅላቸው፣

ከሐዘን፣ ከደስታም ሁሉን አቅምሳቸው፣

ተስፋም በትንሹ ብልጭ አርግላቸው፣

እባክህ ሐሳቤ ለዛሬ እወቅበት፣

ሁሉም ሰው ራሱን አሻግሮ ‘ሚያይበት፣

ሐሳብ ስጠኝና ታሪክ ልፃፍበት፡፡

(ታሕሳስ 9፤ 2004)

Page 17: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

12

“እባክህ ሐሳቤ በሐሳብ ተራቀቅ፣

የሆነች ልጅ ፍጠር ታሪኳ የሚደንቅ”

የሆነም ልጅ ፍጠር በፍቅሯ የሚወድቅ፣

ደስታና ፍሰሃን መሃላቸው ሰካ፣

በአዱኛ ሲሰክሩ አንባቢ እንዲረካ፣

ሳቅ በሳቅ አርጋቸው ዋይታ የታባቱ፣

ሐዘን ደቼ ይብላ ሃሴት ይሁን ቤቱ፣

እባክህ ሐሳቤ ለዛሬ እወቅበት፣

ሁሉም ሰው ችግሩን ስቃዩን ይርሳበት፣

ሐሳብ ስጠኝና ወገን የሚያፅናና ታሪክ ልፃፍበት፡፡

ኖላዊት ሽመልስ

Page 18: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

13

“እባክህ ሐሳቤ በሐሳብ ተራቀቅ፣

የሆነች ልጅ ፍጠር ታሪኳ የሚደንቅ፣

የሆነም ልጅ ፍጠር በፍቅሯ የሚወድቅ''

በናፍቆት ይለቁ አራርቀሃቸው፣

ይራባት፣ ትራበው፣

ይናፍቃት፣ ትናፍቀው፣

ይሂድ፣ ይፈልጋት፣ ያቋርጥ ውቅያኖስ፣

ፍዳውን አሳየው እስኪያገኛት ድረስ፣

ቆማ፣ ተቀምጣ፣ ታልመው ሌት ተቀን፣

መከራዋን ትቁጠር፣ በሐሳብ ትባክን

የአንባቢውን ልብ በስጋት አንጠልጥል

እንደተለያዩ የሚቀሩ አስመስል፡፡

እባክህ ሐሳቤ አንድ ቃል ግባልኝ፣

እንደተለያዩ እንዳትጨርስብኝ፣

እንዲያልቅም አልሻም እኒያ እንደሆኑት፣

እንደነ በዛብህ ልክ እንደነዡልየት::

ብሌይን ከበደ

Page 19: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

14

ምልልስ ፫

ምክር ለሚሰሙ

አታምጣብኝ ስለው አምጥቶ ቆለለው፣

አለ ያገሬ ሰው፣

ሃያ ዓመት በዛብህ እያልኩኝ ስከሰው፣

ጭራሽ እሱ ሕልሙን አርባ አደረሰው?

ቱኒዝን ተመልከት፣ በሃያ ዓመታቸው እንደኮበለሉ፤

ታህሪርን ተመልከት፣ በሠላሳኛቸው እንደተከሰሱ፤

ሊቢያን ተመልከት፣ በአርባ ዓመታቸው አፈር እንደላሱ፤

እኔስ ይሄን ንግርት፣ እኔስ ይሄን ትንቢት፣

ዝምብዬ አላልፈውም፣ አንተም ተማርበት፤

አንተም እወቅበት፣

እንኪያስ ምን ይበጅህ…

በሃያ መኮብለል ወይ በአርባ አፈር መላስ?

በል ተናገር እንጂ፣ የምን ‘መለስ’ ቀለስ!

(ታሕሳስ 14፤ 2004)

Page 20: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

15

እዚህ ቅርብ ነውና፣ የሩቅ አሳቢ አዳሩ፣

በምኞቱ ልክ ይሰንዝር፣ ላይቀር ሳይደርስ ማፈሩ፣

ለማይቀር ቀኑ ሲመጣ፣ በሰፈሩት መሰፈሩ፣

በገባቸው ልክ ያርዱ፣ በክሳቸው ያሸብሩ፣

ቀለም አይዝለቃቸው፣ በድንቁርና ይኑሩ።

ከጥፋት ውሃው ለመዳን፣ ኖህ መርከቡን ሲሰራ፣

አርባ ዓመት አለን ብሎ፥ ነበረ ህዝቡ ‘ሚያሽላላ፤

ወትሮም የሰነፍ ሰው ዕቅድ፣ ስንፍናውን ነው ‘ሚያጎላ፣

አለመስራቱን ነው ‘ሚያሳይ፣ ነውሩን ገላልጦ ካውላላ፤

እንደተቀጡ ያኔ፣ የሃሰት ወሬ ሲነዙ፣ ከነዓንን ሰልለው፣

የገለሞተ በድን ላይ፣ ዛሬም እግዚአብሄር ፈራጅ ነው።

ስለ 1 ቀን 1 ዓመት፣ ስለ 40ው 40ዓመት መዝዞ፣

በድናቸውን ይጣለው፣ በምድረ በዳ አቅበዝብዞ።

አሜን!!!

ዮሐንስ ሞላ

Page 21: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

16

ምልልስ ፬

ምነው ሆዴ…

ገና ለገና ያኔ - በስሜት ሰመመን - በጭንቅ ተይዤ፣

የተናገርኩትን - የገባሁትን ቃል - ድንገት ተናዝዤ፣

እንደቃል አስታውሰሽ - ሲያቀብጥሽ አምነሽ - የምታስጨንቂኝ?

በዚያ ቀውጢ ሰዓት - ነፍስያ ተይዤ - እኔን ብትጠይቂኝ፣

እንኳንስ ቻፕስቲክ - እንኳን ማበጠሪያ - ‹‹ዓለምን ግዛልኝ››

ብለሽስ ብትይኝ?!

እምቢ እንደማይወጣኝ - ለምን አይገባሽም - ከ’ንግዲህ ተረጂኝ፡፡

(ታሕሳስ 17፤ 2004)

በዚህ ቀውጢ ሰዓት፣ በዚህ ቀውጢ ግዜ፣

አንተም ሆንክ እኔ ነፍስያ ተይዘን በወደቅንበቱ፣

አንተም ታውቀዋለህ፤

ገበያ እንውጣ፣ ዓለምን ግዛልኝ ብዬ እንደማልልህ፣

ብጠይቅህ ኖሮ፣.......... እኔ ‘ምጠይቅህ፣

የሰሜኑን ንፋስ ሞገዱን አቁመህ፣

ላንድ ቀን አሳየኝ ነበረ የምልህ፡፡

መሰረት ለማ

Page 22: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

17

እዚያ ላይ…… የጠቀስሽው ቦታ፣

ምን ያህል ብሸልል÷ ምንም ብበረታ፣

በላይን አይደለሁ÷ አሉላ አባነጋ፣

ከቆመ ብረት ጋር ሄዶ የሚላጋ፣

ተላግቶም ሲመለስ÷ ብረቱ ሲጣመም፣

እሱን የማያውቀው÷ ሽንፈትና ሕመም፡፡

ቢሆንም የኔ ቆንጆ…

እንኳን የሰሜኑን ሞገድ÷ ራሴን ‘ምረታበት፣

አቅም የሌለኝ ቢመስልም÷ ችዬ ‘ምቆምበት፣

ችዬ ‘ማቆምበት፣

ሕመም ግን ስላለኝ÷ ሲነፍስ የሸመትኩት፣

አንድም ለመፈወስ፣ አልያም ለመሰዋት፣

እኔም ሞገድ ሆኜ አስከነዳዋለሁ፣

ተስፋ አትቁረጪ እንጂ፣

ደጀን ሁኚኝ እንጂ÷ ቆሜ አስቆመዋለሁ፣

እንኳን ለዚህ ነፋስ÷ መሰረት ለሌለው፣

እምነታችን ካለ፣

ተራራውን ገፍተን÷ እንንደው የለ?!

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

Page 23: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

18

ማንነት ሲረታ በስሜት ትኩሳት፣

በመዋደድ ግለት፣

ዛሬ ላይ ሲፈታ የትላንት፣ የዛሬ፣

የነገ ልዩነት፤

በዚያች ቀውጢ ሰዓት፣ በዚያች ቀውጢ ቅጽበት፣

እንኳንስ አፍቃሪን ፈጣሪንም ማመን፣

ዘበት ዘበት ዘበት!

አንተነህ ተስፋዬ ለማ

አወይ ቀውጢ ሰዓት?......

ላንተ ብቻ አርገኸው ይህን ቀውጢነቱን...

ላንተ ብቻ አርገኸው ይህንን ግለቱን...

ለምን አልደረድር አልጠራ ኮልኮሌ፣

እንደፈለክ ስትሆን በገዛ አካሌ፡፡

- - -

ካልተጋራሁማ ከትኩሳት ግለቱ፣

በራስህ ዛቢያ ላይ ከሆነ ጡዘቱ፣

ቃልህ ከሚጠፋ... በሚለው ልማድ፣

ዓለምንም ቢሆን ትገዛለህ የግድ፣

አንተም የአንተ አፍቃሪ... እኔም ራስ ወዳድ፡፡

ዓለም ተገኝ

Page 24: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

19

ላንበሳ አይመትሩ ለብልህ አይነግሩ፣

ቢሆንም ነገሩ፤

የሸመትከው ሕመም ምንም ሳይበግርህ፣

ጥርግርግ አርጋቸው አውሎ ንፋስ ሆነህ፡፡

የካሣ የልጅ ልጅ ብልሃት አታጣ፣

ንፋሱን አቁመህ ፀሐይ እስክትወጣ፣

እጠብቅሀለሁ፤

ጭጋጉ ተገፎ ያ ቀን እስኪመጣ፡፡

መሰረት ለማ

በዚያ ቀውጢ ሰዓት፣ በዚያ ቀውጢ ቦታ፣

ሰው ሲማረክ ሲሞት፣ በቃላት እሩምታ፤

ሲውነት ሲፈርስ፣ በንክኪ ቃታ፣ በገላ ሰበቃ፣

ዓለም ሲደባለቅ፣ ሲያደነጋግሩ ፀሃይና ጨረቃ፣

አንድም ለመቀየም፣ አንድም ለማስቀየም፣

የአንደበትን ማመን ከቃል ወዲያ ማለም።

መሆኑ እንደታየ...

በዚያ ተራራማ፣ ሰንሰለታማ ሃገር፣

ሞገደኛው ነፋስ፣ ከሰሜን ቢሳፈር፣

ለምን ይፈሩታል? ይሸሹታል ከቶ?

ማለቂያው ሳይታይ፣ አመጣጡ ታይቶ?

Page 25: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

20

ያጋጨን! ያራውጠን! ይበል ያንገዳግደን!

ይሁን ያበጥረን!፣ በደንብ ይበታትነን!...

ብርታት ነው ትምህርቱ፣ ችሎ ካልወሰደ፤

አንድ ቀን ይገፋል፣ መቆም የለመደ።

አንድም ለመለወጥ፣ አንድም ለማናወጥ፣

ነፋስ ሲበረታ፣ ሿ...ብሎ ሲመጣ፣

ተስፋ አዝሎ ሰንቆ፣ ነጋሪት ሲመታ፣

ነቅቶ ሲያነቃቃ፣ አግስቶ፣ ሲያስገሳ፣

ችለው ካደመጡት፣ ሲያስጮህ ድብ አንበሳ፣

ቆርጠው ሲታገሉት፣

ታግለው፣ ሲቋቋሙት፣

ተጋፍተው፣ ሲገፉት፣....

ያበረታል እንጂ፣ ነፋስ መች ይወስዳል?

ከተራሮች ጋራ ባንድ ካላበሩ፣

ከሚበሩት ጋራ ባንድ ካልበረሩ፣

ከነፋሳት ጋራ ባንድ ካልመከሩ፣

የነፋስ እሩምታ፣ መች በቃል ይቆማል?

እርኩስ መንፈስ አይደል፣....

በስመ አብ...ቅዱስ፣ ካሣ፣ ቢሉት መች ይበራል?

Page 26: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

21

ባይሆን፣ "ዘራፍ" ብለው፣

የቴዲን ዓላማ፣ ራእይ ሲሸክፉ፣

ባንድ ላይ ሲያብ’ሩ፣

አውሎ ነፋስ ሆነው፣ በፅናት ሲጋፉ፣

ንፋሱም ይሸሻል...!

ተራራም ይገፋል...!

ፍቅርም ይደረጃል...!

እናት ቤት ይሞቃል...!

ቃልም ይጠበቃል...!

እምነትም ይፀናል...!

ዓለምም ይገዛል...!

!!!

ዮሐንስ ሞላ

Page 27: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

22

እናቷ ሳይነገራት ተድራ፣

አስከፊ ኑሮ በመኖሯ፣

ልጇ…

የራሷን የትዳር ዕድል፣

በራሷ መወሰን እንድትችል፣

ታገለች፡፡

ታግላም አልቀረች…

ታደለች፡፡

ይኸው ልጇ የራሷን ዕድል፣

በራሷ ልትወስን እስከመገንጠል፣

እስከመገነጣጠል…

እስከመዘነጣጠል፣

እስከመነጣጠል፣

ከጋብቻ እስከፍች፣

ለመብቃት ደረሰች፣

እናት ግን ተከፋች፡፡

“ሕልሜን በልጄ ውስጥ÷ አያለሁኝ” ብላ

እንዳማራት ቀረ÷ ባይኗ እንደተጉላላ፡፡

(ታሕሳስ 20፤ 2004)

Page 28: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

23

እምነት ሲለካ

ቃልኪዳን ተጋብተን÷ አስሬልሽ ኒካ

ትራ*ስ formatioኑን÷ አብረን ልናሳካ

ጥለሽኝ ስትሄጂ÷ በዲቪ አሜሪካ

ያንን ሁሉ ትግል÷ ያንን ፖለቲካ

ቻው በለው አሰኘኝ÷ ‘ሸለለ ፑቲካ፡፡’

(ታሕሳስ 25፤ 2004)

ደሴ እና DC

DC የከተመው÷ የደሴው ሽብሩ፣

ስሙ ተቀይሮ÷ ተብሎ Andrew፣

አገር ቤት ደውሎ÷ ወንድሙን ሊያናግር፣

ተጣልተው የቀሩት÷ እንዲህ በሚል ነበር፡፡

የደሴው…

አልመጣም አንተዬ፣

አንተን ተከትዬ፣

እናቴን ቻው ብዬ፣

እት ወንድሜን ጥዬ፡፡

Page 29: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

24

የDCው…

የድህነት ተባይ፣

የአለማወቅ ስቃይ፣

አናትህ ሲወጣ፣

ወደህ ነው ‘ምትመጣ?!

የደሴው…

በሳይንስ ቀመር÷ ከሚ’ሠራ ቋንጣ፣

ጦሳ ያበቀልኩት÷ ይምጣብኝ ሰላጣ፡፡

ከኒውዮርክ አይጦች÷ ከለንደን በረሮ፣

የአገሬ ቁንጫ÷ ይንከሰኝ አምርሮ፡፡

ከዘመነው ሐኪም÷ መቅደድ ከሚያውቅበት፣

የአጥቢያዬን ጠበል÷ እንዳፈጣጠሬ…ልንቦራጨቅበት፡፡

ከደም ቅዳ መልስ፣ ማደንዘዣ መርፌ፣ ኪኒን ምናምንቴ፣

በአረቄ አስለምልማ፣ማሰሻ ተኩሳ፣ ታድነኝ እናቴ፡፡

የDCው…

አይ የኔ ወገኛ÷ ኩራት ያስለመደህ፣

ችጋር፣ ማይምነት÷ እንዲህ ካስደተህ፣

ሲያሻህ ተጋብተኸው÷ ሲያሻህ ተዋልደህ፣

አዝለኸው እየዞርክ፣

እዚያው በጠበልህ÷ መኖር ትችላለህ፡፡

የደሴው…

የፈረስ ጥርስ አጥቦ÷ ጥሪት ማጠራቀም፣

የባዕድ ደጃፍ ላይ÷ ትርፍራፊ መልቀም፣

ቢቀርም አይጎዳ÷ ኖሮም አልጠቀመም፡፡

Page 30: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

25

ይልቅስ..

የመኖር ትርጉሙ ÷ ጣፍጦ ‘ሚጣጣመው፣

በ‹ስንት ያዘ?› ሳይሆን÷ በ‹ስንት ኖረ?› ነው፡፡

አንተ መፃተኛ÷ የሰው አገር ስትዞር፣

ወይ ታሪክ አትሠራ÷ ወይ ኖረህ አትኖር፣

መምጣትህ አይቀርም÷ ሞተህ ልትቀበር፤

እኔም ያንተ ወንድም÷ የማልጨክንብህ፣

እጠብቅሃለሁ÷ አልቅሼ ልቀብርህ፡፡

***

ስልኩን ጥርቅም አርጎት÷ አንድሩ ተናዶ፣

ተኳርፈው ሲኖሩ÷ ብዙዓመታት ነጉዶ፣

ኩርፊያውን ሊሰብር፣…

ናፍቆቱንም ሊሽር…

ላጤው የDC ሰው ዶላሩን አሟጦ፣

ብዙ ሺኅ ማይሎች÷ በበረራ አቋርጦ፣

አንድ የቀን ማለዳ÷ በደሴ ከተማ፣

ከች አለ እየነዳ÷ ባላራቱን ጎማ፣

ገበሬው ወንድሙም÷ ይህን እንደሰማ፣

በጋሪ እና ባጃጅ÷ መጣ ከንፎ፣ ከንፎ፣

አራት ልጆች እና አራት ተስፋ አቅፎ፡፡

(ጥር 13፤ 2004)

Page 31: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

26

ገዢና ተገዢ

ሻጭም ሸጦ እንዲያተርፍ÷ ገዢም እንዲገዛ፣

ሸጠው፣ አሻሽጠው÷ ይግዙን እንደዋዛ፣

መግዛትና መሸጥ፣

ሲመችም ማሻሻጥ፣

ተገዢ ባለበት፣

ምን ነውር አለበት?

(ጥር 15፤ 2004)

ተገዢና ገዢ

አንተን መግዣው÷ ብልሐቱ፣

ማሰሪያው፣ ሰንሰለቱ፣

ድንገት አፈትልኮ÷ በጠላትህ እጅ ቢወድቅም፣

በወደቅክበት እየረገጠ÷ ቢያሳጣህም አቅም፣

የገዥን ቀንበር ሰባብሮ÷ ዳግም ነፃ ለመውጣት፣

በልብህ ያለውን ፍርሃት፣ የተገዥነት ቅንጣት፣

ሙልጭ አድርጎ ለማንፃት፣

ነፍጥና ምሳር ሳይሆን÷ ቆራጥ ልብ ነው የሚያሻህ፣

ዝምብሎ መታዘብ ሳይሆን÷ እምቢኝ ማለት ነው ‘ሚያዋጣህ፣

ምንም ገዢና ሻጪ÷ ቢስማሙ በራስህ ጉዳይ፣

አልገ’ዛም ብለህ ከመረርክ ማነው ደፍሮ አንተን የሚያይ?፣

በል አሻፈረኝ በል÷ ‹‹ምረር እንደቅል፣

ባለመምረሩ ነው÷ ዱባ ‘ሚቀቀል፡፡››

(ጥር17፤ 2004)

Page 32: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

27

የምርጫ ቅስቀሳ

ዓለምዬ፣ ዓለሚቱ፣

የሺ ሐረጊቱ፣

ያላንቺ ካሠቡት÷ “እንኳን አብዮቱ፣

አይነጋም ለሊቱ፡፡”

ካገባሽኝ…እቱ፣

እንኳን ቀኑን ቀርቶ÷ ጣይ ያለችበቱ፣

ብራ ነው ለሊቱ፡፡

ሌሎች ወንዶች ሁሉ÷ ወደድኩ የሚሉቱ፣

ሁሉም ከንቱ፣ ከንቱ፣

እኔን ካየሽ… እቱ፣

የተዘፈነልኝ ዘፈን በያይነቱ፣

እያሉ “ውበቱ፣

ዕውቀት፣ ደግነቱ፣

ደሞዙ ብዛቱ”

ካገባሽኝ… እቱ፣

ጫጉላሽ ሐሴቱ፣

ተድላ ሙሉ ቤቱ፣

ልጆች ሲጫወቱ፣

በቂ ነው ማየቱ፣

እንኳንስ ማግኘቱ፡፡

ይሄ ምድረ ገልቱ፣

አንቺን መመኘቱ፣

ድፍረቱ፣ ንቀቱ፣

ከኔ ወዲያ ላንቺ÷ አወቅኩ ማለቱ፣

ተይው ምናባቱ፣

እኔን አግቢኝ እቱ!...

***

Page 33: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

28

(የምርጫው ማግስት…)

ሂጅ ወደዛ ሂጂ፣

ወደሽኝ፣ ወድጄሽ አገባሁሽ እንጂ፣

ልታስሪኝ ነው እንዴ?

ኧረ ወይኔ ጉዴ!

ወሸምኩኝ አበጀሁ፣ ወሰለትኩ አበጀሁ!

ቅናት አያብግንሽ÷ ወዳጅ ስላገኘሁ፡፡

ሂጅ ወደዛ ሂጂ፣

ወደሽኝ ወድጄሽ፣ አገባሁሽ እንጂ፣

ተሸክሜሽ ልኖር ቃል ገባሁኝ እንዴ?

ኧረ ወይኔ ጉዴ!

አንደዜ ሹመሽኝ÷ ባለቤት አድርገሽ፣

ቀና ብለሽ ደሞ÷ ደፍረሽ ታዪኛለሽ?

አወይ ሁሉ አማረሽ!

***

እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ያገሬ ጫወታ፣

“ምረጡኝ” ብለውን÷ የመረጥን ለታ፣

‘ትርፉ… እርግጫ ነው÷ ያህያ ውለታ’፣

በይ ተመልካችነት÷ በራስህ ገበታ፡፡

እስር ቤት ነው’ንጂ÷ ቤት አይመታም ግጥሙ፣

ካቴና ይሆናል÷ ቀለበት ትርጉሙ፡፡

(ጥር 23፤ 2004)

Page 34: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

29

የደም ውርስ

የኔው አባት ጌታ÷ የኔው አባት አሽከር፣

ሁሉን ባንድ ጫንቃ÷ ተሸክሞት ነበር፡፡

ደሙ ተመንዝሮ÷ በውልደት፣ ጋብቻ፣

ባላባትና አሽከር÷ የስልጣን ሽኩቻ፣

ንክሻ፣ ቡጥጫ…

እየተቧደኑ÷ ሌላውን ጥላቻ፣

ሁሉን ሆኖ ኖሯል÷ ስለመሆን ብቻ፡፡

ግዴለም… ግዴለም…

በነበር መሸበር÷ ለኔም ደግ አይደለም፡፡

* * *

ያለፈው፣ ያላለፈው’ና የምናልፍበት ሲታሰበኝ፣

የሆንነው፣ ያልሆንነው’ና የምንሆነው ሲታለመኝ፣

የሚያሳዝን፣ የሚያስተክዘኝ’ና ጭንቅላቴን የሚንጠኝ፣

አለፈ ያልኩት፣ እያላለፈ÷ ይሆናል ያልኩት እየቀረ፣

ያባት ዕዳ ለልጅ፣ የልጅም ለልጅ ልጅ÷ ይቀጥል ጀመረ፡፡

(የካቲት 4፤ 2004)

Page 35: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

30

ከቃሌ እና ልቤ

እኔ ስለወደድኩሽ÷ ፍፁም ላትለወጪ፣

ጨረቃን ላትመስይ÷ ከከዋክብቱ ላትበልጪ፣

በቅኔ ሽሙንሙን÷ በውብ ቃላት ድርደራ፣

በአፌ ማጭበርበር÷ ልብሽ ለልቤ ቢራራ፣

እውነቱን ያወቅሽ’ለት÷ ሰው የመሆንሽን፣

ሰው የመምሰልሽን፣

በአፌ እንዳመጣሁሽ÷ በአፌ አላቆይሽም፡፡

ወደድሽም፣ ጠላሽም÷ አልሸነግልሽም፣

ከሙገሳ ወዲያ፣

መውደዴ ካልገባሽ÷ ፍቅሬ አይገ’ባሽም፡፡

(የካቲት 4፤ 2004)

Page 36: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

31

የአንድነት ቀኖና

ሰዎች እንደሚሉት፣

አንድ አምሣል፣ አንድ አካል÷ አንድ ሰው ሁነናል፡፡

እኔ ግን የምለው፣

እንኳን አንድ ልንሆን÷ ተቃርነን ቀርተናል፡፡

ሲጀምር፤

እኔ ወንድ፣ አንቺ ሴት÷ ምን አንድ ያደርገናል?

ሲቀጥል፤

እኔ ምስራቁን ሳይ÷ ዓይንሽ ምዕራብ አርፏል፡፡

ሲሠልስ፤

የኔ አፍ ሲያወራ÷ ያንቺ ግን ዝም ይላል፡፡

እነርሱም ይላሉ፣

የእርሷን ጎዶሎ÷ ያንተ ትርፍ ይሞላል፣

የአንተ ዓይን እርሷን÷ የሷም አንተን ያያል፣

እርሷ ስታዳምጥ÷ ያንተ አፍ ያወራል፡፡

አንድ መሆን ማለት÷ በዓይነት አይደለም፤

በድምር ካልሆነ፤

ጎዶሎነት እንጂ÷ አንድ መሆን የለም፡፡

የለም፣ የለም፣ የለም፡፡

(የካቲት 11፤ 200 4)

Page 37: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

32

ፋኖሴ

እናት ነሽ ይላሉ÷ እናቴ አይደለሽም፣

እህት ነሽ ይላሉ÷ እህቴ አይደለሽም፣

ሚስት ነሽ ይላሉ÷ ሚስቴም አይደለሽም፣

የዝምድና መጥበቅ÷ የልብ አያደርስም፡፡

ዝምድና እንደ ምንጭ÷ ከውስጤ አይፈልቅም፣

ተቆርጦ ‘ሚቀጠል÷ ጋብቻ አልፈልግም፡፡

እራሴው ልንገርሽ÷ ማንነትሽን እንቺ

ዓለም ያየሁብሽ÷ ዓይኖቼን ነሽ አንቺ፡፡

(የካቲት 24፤ 2004)

ለከንፈር ወዳጄ

ከንፈርሽን ስስምሽ፣ ጡትሽን ስዳብስሽ፣ የሚሰማኝ ስሜት

የሚያንዘረዝረኝ - እሱኛው አይደለም፤ ለኔ ፍቅር ማለት

ለኔ ፍቅር ማለት….

ስደሰትና ሲከፋኝ፣ ወይም ደሞ ግራ ሲገባኝ

የሆነው ሁሉ እንደሆነ፣ መደናበሬም ሳይለቀኝ

ልቤ ደውል ሲለኝ፤ ቅጠር፣ ሂድ አግኛት

ሁሉንም አጫውታት፣ መፍትሄህ እሷው ናት

ብሎ ሲሰቅዘኝ፣ እያለ ንገራት፡፡…. ንገራት፣ ንገራት፤

ያ’ነው ለኔ እንግዲህ÷ ፍቅር ያዘኝ ማለት፡፡

(የካቲት 27፤ 2004)

Page 38: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

33

እስኪ ጽደቁብኝ

ሀገሬው የዋህ ነው፤ ይታመናል ብዬ፣

የልቤን ደጃፉን÷ ሳልቆልፈው ውዬ፣

ከአንዱ አጥንት ወስዶ÷ የፈጠራት አንዷ፣

ዘው ብላ ገብታ÷ በገዛ ፍቃዷ፣

በፈገግታ ሽፋን፣ በስርቆት እይታ፣

ልቤን ሰርቃው ሄደች÷ በአፍታ ቆይታ፡፡

---

እንደኔዋ ሌባ÷ የሚያ’ውቅበት መስረቅ፣

ትርፍ ልብ ያለው ሰው÷ ይስጠኝና ይጽደቅ፡፡

(መጋቢት 1፤ 2004)

R.I.P.

ሆድ እስኪፈነዳ÷ ቢበሉ፣ ቢጠጡ፣

የስልጣን አቀበት÷ ሺ ግዜ ቢወጡ፣

ከንቱ ሕልም አይሞላም÷ ምን ቢቀላውጡ፤

በታሪክ አዲስ ባይሆንም÷ ሞት ለነዚህ ዓይነቱ፣

ነፍስ ይማር ይባላል እንዴ÷ ሲሞቱ ኖረው ለሞቱ?

(መጋቢት 4፤ 2004)

Page 39: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

34

መንገድ

እሁድ ባ’ራት ሰዓት፣ ከቤቴ ወጥቼ፣

በስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አርግቼ፣

ለገሃር ለመድረስ ስጣደፍ ጓጉቼ፣

እሷም ባ’ራት ኪሎ ወደቦሌ ልትሄድ፣

በአንዲት ታክሲ ውስጥ አገናኘን መንገድ፡፡

ጉዞን ስንጀምረው ገና ካ’ራት ኪሎ፣

ዘላለም የማያልቅ ትልቅ መንገድ መስሎ፣

አዋዶን፣ አዋርቶን ቃልም አስገባብቶ፣

ያገናኘን መንገድ አጉል ተስፋ ሰጥቶ፣

መስቀል አደባባይ፣ መስቀል ሐሳብ ወልዶ፣

እሷን ተከትሎ ወደቦሌ መንደር፣

አሊያም እኔን ብሎ ለገሃር መሻገር፣

ወይም ለየብቻ ተለያይቶ መብረር፣

አሊያም ቆሞ መቅረት፣ ሌላ ምርጫ ነበር፡፡

---

መስቀል አደባባይ እግዚአብሔር ይይልህ፣

አራት ትርፍና አራት ኪሳራ አዝለህ፣

አንተ ተከፋፍለህ፣ ልብ ትከፍላለህ፡፡

(መጋቢት 8፤ 2004)

Page 40: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

35

የጾም ጥብስ

ነገሩን ‘ሀሁ’ ብለን ስንጀምረው

‘ጠበስኳት’ ብዬ ነበር የምናገረው

ግና እያደርኩ ስታዘበው

የተጠበስኩ እኔው ራሴው፡፡

(መጋቢት 10፤ 2004)

ስልጣን እንዲቀና

ባይገባችሁ’ንጂ ባትረዱት፣

ቀምሳችሁ ባታጣጥሙት፣

ከላይ’ኮ ለተቀመጡት፣

መውረዱ ቀላል አይሆንም÷

በቀላሉ ስለማይወጡት፡፡

- - -

እንደመፍትሔ…

አንድ ግለሰብ ከሚሆን÷ ባለ በትረ ስልጣኑ፣

አስጨብጦ መገላገል÷ ለሕዝበ ብዙሐኑ፡፡

(መጋቢት 14፤ 2004)

Page 41: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

36

ትዝታ ዘ ሚያዚያ 30፤ 1997

አለብኝ ትዝታ፣

ልብን የሚረታ፡፡

ሚያዝያ ሲመጣ፣

እምባ የሚያመጣ፣

መስቀል አደባባይ፣

በዚሁ ከተማ፤

ያወጣሁት ግጥም፣

ያወረድኩት ዜማ::

እንዴት ይረሳኛል፣

የሮጥኩት ሩጫ፣

የመረጥኩት ምርጫ፡፡

አለብኝ ትዝታ፣

ልብን የሚረታ፣

ውስጥ ውስጡን የሚቆጭ፣

ደግሞ የሚያበረታ፡፡

(መጋቢት 21፤ 2004)

Page 42: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

37

ራስን ፍለጋ

ከተሰለፍኩበት÷ በወል ተሰድሬ፣

በወግ ተሰናድቶ÷ ካማረው ነገሬ፣

ሰሜንና ወርቄን÷ ወዲህና ወዲያ፣

ነጣጥሎ ያስቀረኝ÷ ያላንድም እኩያ፣

ማነው ገጣሚዬ÷ አሳስቶ የጻፈኝ፣

ወርቅ ነኝ እያልኩት÷ በሰም የለበጠኝ?

ማነው ምቀኛዬ - ነጥሎ ያወጣኝ÷ ከስንኞች ተርታ

ሰው ከሚኮንበት÷ ቤት ከመድፊያው ቦታ፡፡

(መጋቢት 25፤ 2004)

ይደነግጣል ልቤ

ቆንጆ ባየሁ ቁጥር - ቁመቷ ያማረ፣

አሳምሮ ሰርቷት - ደምግባቷ የሰመረ፣

ይደነግጣል ልቤ - እየተታለለ፣

አምና የሄደችው - ከየት መጣች እያለ፡፡

(መጋቢት 27፤ 2004)

Page 43: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

38

“ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሣ ብሎ ስም፣”

አምና ነበር’ንጂ ዘንድሮ የለም፡፡

- - -

ጀግና ወልዳ ወልዳ ጀግና እየገደለች፣

በገዛ እጇ እናቴ መሃን ሆና ቀረች፡፡

- - -

ትመጪልኝ እንደሁ ዛሬ ነይልኝ፣

በዚህ አኗኗሬ ነገን እንጃልኝ፡፡

- - -

ተበደልኩኝ ብለሽ ወደኔ እንዳትመጪ፣

እዛው ባለሽበት እራስሽን ነፃ አውጪ፡፡

- - -

ሰሚ በሌለበት ምንም እንዳትይ፣

ቀድሞ የታሰረ ይታሰራል ወይ፡፡

- - -

በሕሊና እስራት ከምንሰቀቃይ፣

ትንሳኤን አስታከው መምሬአችን ከላይ፣

ይፍቱን እባክዎ ለዛሬስ አንድላይ፡፡

(ሚያዝያ 4፤ 2004)

Page 44: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

39

ይብላኝ ላንቺ

የምቀበል እንጂ፣ እሰጠው የሌለኝ÷ እኔ ምስኪንተኛ፣

አንቺ ራስሽ ድሃ፣ ዓለም ያወቀልሽ÷ ያገር ምፅዋተኛ፣

ታዲያ አብረን ስንኖር÷ ከመላቀስ በቀር፣

ንገሪኝ ምንድን ነው÷ ያፈራነው ነገር?

ሲርበኝ ታበዪኝ፣ ስታረዝ ታለብሺኝ፣

ስታመም ታድኚኝ፣ ስቦርክ ታስጠጊኝ፣

ካልቻልሽ አንቺ ጋራ÷ የሚያኖር ምን አለኝ?

የሌለኝን መቁጠር÷ ይቀላል መሰለኝ፡፡

* * *

ስለዚህ ልሄድ ነው፤ ጥዬሽ ልሰደድ፣

ላንቺ ያለኝ ፍቅር፣ ላንች ያለኝ መውደድ፣

ሲርብ አይበሉትም፣ አይጠረቃም ሆድ፣

ስመሽ አሰናብቺኝ÷ ይልቅስ ልሂድ፡፡

* * *

ኑሮዬን ፍለጋ ከወጣሁበቱ፣

ምግብና ምቾት ከሚበዛበቱ፣

ከወዲያኛው ዓለም ከሄድኩኝ በኋላ፣

ልመለስ ቃል አለኝ፣…

ወይ ኑሮሽ፣ ኑሮዬ ያንዳችን ከሞላ፡፡

አንቺስ እናት ዓለም?

ጥሪት ስቀራርም ከርሜ እስክመጣ

ትጠብቂኝ ይሆን÷ እስኪ ቃልሽ ይውጣ?

* * *

Page 45: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

40

ምነው፣ ምነው፣ ምነው?

ፊትሽ ከፋው ምነው?

ኢኮኖሚሽ አድጎ፣ እጅግ ተመንድጎ፣

በሁለት ዲጂት÷ ትራንስፎም አርጎ፣

አባይ ተገድቦ÷ ምድርሽ ብራ ሆኖ፣

መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ ሰፍኖ፣

ለጋሽ የሆንሽ እንደሁ÷ ምፅዋት መሻት ቀርቶ፣

እንኳን እኔ ልጅሽ÷ ማን ይቀራል ከቶ!?

* * *

ግና የሚያሰጋኝ የነገሬ ወጉ፣

ይሄ ሁሉ ያልኩሽ ማደግ መመንደጉ፣

አሁን ባለው ሂደት በዚህ አያያዝ፣

በበሬ፣ ገበሬ፣ በድሃ ደም ወዝ፣

የገነቡት ሕንፃ፣ የገነቡት ቤት፣

እስኪ ልጠይቅሽ፣ ልማት ነው ጥፋት?

(ሚያዝያ 5፤ 2004)

Page 46: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

41

ከዚህና ከዚያ

አገሪቷን በወንዝ - ተራራ እና ገደል - ምስል ያስቀራችሁ ፣

እነ ማሞ ቂሎ - እነማሚት ሞኚት - እንዴት አደራችሁ?

አገር ሲሉ…

አፈር ወደሰማይ ቢቆልሉ፣

ድንጋይ ሽቅብ ቢከምሩ፣

የዕንቁ ጉድጓድ ቢቆፍሩ፣

የወንዝ መዓት ቢገድቡ፣

ሺኅ መፈክር ቢያነግቡ፣

የማይገልፁት ቃል ነው - እልፍ ጥበብ ቢታደሉ፣

ሳስቆ ‘ሚያድርበት - ሁሉ እንደያ’መሉ፡፡

***

የአገር ፍቅር ማለት - ስለአገር ማውራት - በአገር እየኖሩ

ነው ያላችሁቱም - ፍቅር እስክታውቁ - በሉ ደህና እደሩ፡፡

የአገር ፍቅር ሲሉ…

በመንፈስ ተሰደው ሳሉ፣

በአካል ብቻ እዚህ ላሉ፣

አገር ቤት እየኖሩ፣

የሕዝብ ካዝና ለሚሰብሩ፣

በአገር ስም እየማሉ - በአገር ለሚቆምሩ፣

ምናቸውም አይደለ - አይገባቸውም ምስጢሩ፡፡

***

Page 47: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

42

የአገር ፍቅርስ ማለት…

እግራቸው ባህር ማዶ ረግጦ፣

አካላቸው ሰው አገር ተቀምጦ፣

የአገር ቤት ዜና ካላዩ - ዜና ያዩ ለማይመስላቸው፣

እናት ጦቢያን ሲያስነጥሳት - እነርሱን ለሚቆርጣቸው፣

በልግ ደረቀ ሲባል - ወገን ሳይራብ ለሚርባቸው፣

ሄደው እንኳን ላልሄዱ - መመለሻም ለሌላቸው፣

ናፍቆት እንደልጅ አዝለው - እረፍት ለማያሻቸው፣

ለነዛ ምስኪን ስደተኞች - ኑሮና ዘመን ለገፋቸው፣

አዎ! የአገር ፍቅርስ ማለት… ለነርሱ ብቻ ነው ‘ሚገባቸው፡፡

(መታሰቢያነቱ፡- በተለይ ለማሕሌት ሰለሞን - ሚያዝያ 12፤ 2004)

Page 48: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

43

ተዉ አትፍረዱበት

ከሰው በላይ የእርሱ ደምቆ እንዲታይለት፣

የፊቶቹን ስሞች ማጥፋት ነበረበት፡፡

(ሚያዝያ 12፤ 2004)

ስለኔ ይወራል አሉ?

ገጣሚ ነህ ይሉኛል፣

እኔም አንዳንዴ ይመስለኛል፣

ግን ጮክ ብዬ ሳስበው፣

የሚገባኝ እንዲህ ነው፡፡

አንዳንዴ… ቤት የሚመታ፣

አንዳንዴ… ምንም የማይመታ፣

እኔም ራሴ ግጥም ነኝ፣

የማላውቀው እና፣

እሱም በቅጡ የማያውቀኝ፣

አንዱ ገጣሚ የጻፈኝ፡፡

(ሚያዝያ 17፤ 2004)

Page 49: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

44

ያለውን የሰጠ

ገጣሚ አይደለሁም፤ ቃል ከቃል ሰክቼ አላወድስሽም፣

ዘፋኝም አይደለሁ፤ ዜማ እያንቆረቆርኩ አላስደስትሽም፣

ቀራጭም አይደለሁ፤ ምስልሽን ቀርጬ አላቆምልሽም፣

ሃብታምም አይደለሁ፤ ወርቅ አምባር ገዝቼ አላጠልቅልሽም፣

ጡንቸኛም አይደለሁ፤ በአቋሜ ኮርቼ ላኮራሽ አልችልም፣

ሰው ፊት የሚያቀርቡት ጥሎሽ ባይኖረኝም፣

እንቺ መውደድ ውሰጅ…

የማያልቅ ፍቅር መስጠት አይከብደኝም፡፡

(ሚያዝያ 19፤ 2004)

ባይተዋርነት

እቅፏ ውስጥ ሆኜ÷ ሰርክ እየበረደኝ፣

ጣት ጣቷን እያየሁ÷ ጉርሻዋ እያማረኝ፣

የማቀነቅነው በቃላት፣ በዜማ÷ ፍቅሯ እየናፈቀኝ፣

አለችኝ እላለሁ÷ በመንፈስ ሳትኖረኝ፡፡

የተሸለለላት፣ የተዘፈነላት፣

ጀግኖች በጎራዴ የተጋጠሙላት፣

አንገቴ፣ ሕይወቴ÷ ይሰዋልሽ ያሏት፣

ዛሬስ ናፈቀችኝ÷ አገሬ ወዴት ናት?!

(ሚያዝያ 25፤ 2004)

Page 50: የፌስቡክ ትሩፋት (Ye'Facebook Tirufat)

የፌስቡክ ትሩፋት

45

በመጨረሻ…

ማን ጉድጓዱን ይማስ፣

ማን አፈሩን ያልብስ፣

ማን ቆሞ ያስለቅስ፣

ማን ደረቱን ይድቃ፣

በዛሬው ሰቆቃ….፡፡

***

ማን ተዝካር ይደግስ፣

ማን ይማፀን ለነፍስ፣

ማን ሃውልት ይገንባ፣

ማን ያኑር አበባ፣

ማን ፍታቱን ይፍታ፣

ልክ እንደዘንድሮ÷ ሕዝብ የሞተ’ለታ፡፡

(ሚያዝያ 27፤ 2004)

? ? ?

አንተ እዚያ ማዶ÷ ግራ ጥግ ያለኸው

የነገር ቋጠሮህን÷ ስበኸው ስበኸው

የኔን መካከለኛ÷ ቀኝ ጥግ አሰኘኸው

- - -

እንደዚህ ሲጎተት÷ ይሄ የነገር ቋጠሮ

የተበጠሰ እንደሆን÷ አላግባብ ተወጥሮ

አንተንም እኔንም ነው÷ የሚጠብሰን ዞሮ፣ ዞሮ፡፡

(ነሐሴ 15፤ 2004)