Ossa-bcc Kit Final

Post on 08-Apr-2015

533 views 0 download

Transcript of Ossa-bcc Kit Final

የባህሪ ለውጥ መግባቢያ ኪት

አዘጋጅ፡

ውብሸት ታደለ (ዴር ኮንሰልታንት)

መስከረም 2002 ዓ.ም

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

2

መቅድም

ይህ ኪት በኤች አይ ቪ ዙሪያ መሰረታዊ መረጃዎች

የተካተቱበት የመረጃ መድብል ሲሆን በህፃናት ላይ በሚደርስ

መገለልና መድልኦ ዙሪያ እንዲያተኩር ተደርጎ የተዘጋጀ

ነው።

ኪቱ በኤድስ መከላከያና ማህበራዊ አገልግሎት ድርጅት

(OSSA) እና የዴንማርክ ህፃናት አድን ድርጅት (Save the

Children-Denmark) ትብብር የተዘጋጀ ነው።

ኪቱ የተዘጋጀውና የተቀናበረው በዴር የማህበራዊና ስነ-

ልቦናዊ ጉዳዮች አማካሪ ድርጅት (DARE Consultant)

ነው።

በመጨረሻም ለዚህ ኪት ዝግጅት መሳካት የበኩላቸውን

ላደረጉ ሁሉ ምስጋና ይድረስ!

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

3

ማውጫ

መግቢያ ----------------------- 5

የኤች አይ ቪ ምንነት ------------- 7

ኤች አይ ቪን መከላከል ------------------ 13

ህይወትና ባህርይ ------------------- 17

ኤች አይ ቪና የወሲብ ባህርይ ------------------ 19

የኤች አይ ቪ መተላለፊያ መንገዶች ----------- 24

ኤች አይ ቪ የማይተላለፍባቸው መንገዶች -----32

ኤች አይ ቪ እና ማህበራዊ ችግሮች -------- 36

ኤች አይ ቪ፣ስርዓተ-ፆታና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች- 39

አደገኛ ዕፆች፣ አልኮልና ኤች አይ ቪ ------ 53

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

4

የበጎ ፈቃድ የስነ-ምክር አገልግሎትና ኤች አይ ቪ - 60

የስሜት ልዕልና/ማዕምር -------------- 71

ስለ ሌሎች ማሰብ (Empathy) -----------------72

መገለልና መድልኦ ----------------79

የመገለልና መድልኦ ዓይነቶች ------ 81

መገለል፣ መድልኦ እና ህፃናት ------- 88

የመገለልና መድልኦ ውጤቶች ----- 95

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

5

መግቢያ

ይህ ኪት በኤች አይ ቪ/ኤድስ ዙሪያ መሰረታዊ

የሚባሉ መረጃዎችንና የባህርይ ለውጥ ለማምጣት

የሚያግዙ አቅጣጫዎችን አካቶ የያዘ ሁለ-አቀፍ

የመረጃ መድብል (Information Education &

communication /Behavioral Change Communication Kit)

ነው።

ኪቱ ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን

መገለልና መድልኦ አተኩሮ መረጃ የሚሰጥና

አስፈላጊው የባህርይ ለውጥ እንዲመጣ መከተል

ያለብንን አማራጭ መንገዶች የሚያመላክት ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

6

በኪቱ ውስጥ የተካተቱትን መረጃዎች ለሌሎች

በማሰራጨትና እንዲያውቋቸው በማድረግ የመረጃ

ተደራሽነቱን ማስፋት ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር

ነው።

በዚህ IEC/BCC ኪት ውስጥ የተካተቱትን ነጥቦች

ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ መረጃዎችን መሰብሰብና

የዕውቀት አድማስን ማስፋት ያስፈልጋል።

መልካም ንባብ!

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

7

የኤች አይ ቪ ምንነት

የአለም ጤና ድርጅት የኤድስ ፕሮግራም ዳይሬክተር

የነበሩት ጆናታን ማን ኤች አይ ቪ ሶስት የክስተት

ደረጃዎች እንዳሉት ያብራራሉ።

አንደኛ፤ የቫይረሱ የክስተት ደረጃ ወይም የኤች አይ

ቪ ክስተት ሲሆን ይህም የሰው ልጅን የበሽታ

መከላከያ አቅም የሚያዳክም Human Immune

Deficiency Virus የተባለ ሰውን ብቻ የሚያጠቃ

ቫይረስ በደም ውስጥ መከሰቱን የሚያመለክት ነው።

ኤች አይ ቪ በማንኛውም ዓይነት ሰው ውስጥ ሊከሰት

የሚችል እና ባህሪው ከሌሎች ተውሳኮችም ይሁን

ከቫይረሶች ይልቅ አስቸጋሪና ተለዋዋጭ ከመሆኑ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

8

የተነሳ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችል

መድሃኒት ያልተገኘለት ነው፡፡

አንድ ሰው በደሙ ውስጥ ኤች አይ ቪ ተገኘበት

ማለት በሽታን ለመከላከል የሚያስችለውን አቅም አጣ

ማለት አይደለም። ለበሽታ ወይም ህመም የሚጋለጠው

ወደ ቀጣዩ ደረጃ ሲሸጋገር ነው።

ቀጣዩና ሁለተኛው ደረጃ የኤድስ ደረጃ ነው። ኤድስ

ከእንግሊዝኛ የተወሰደ ምህፃረ ቃል ሲሆን

እንደሚከተለው ሊተነተን ይችላል፡

AIDS:

A=Acquired

I=Immune

D=Deficiency

S=Syndrome

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

9

Acquired ማለት አብሮን ያልተፈጠረ ወይም ያልቆየና

ከሌሎች የመጣ ወይም የተላለፈ ማለት ነው።

Immune ማለት የሰውነታችን በሽታን የመከላከል

አቅም ወይም የበሽታ መከላከያ ማለት ነው።

Deficiency ማለት እጥረት ወይም መመናመን ማለት

ነው።

Syndrome ማለት የበሽታ ምልክቶች ጥርቅም ማለት

ነው።

ስለዚህም ኤድስ በኤች አይ ቪ ምክንያት የበሽታ

መከላከያ አቅማችን ሲመናመንና ሲዳከም የሚከሰት

የተለያዩ የበሽታ ምልክቶች ወይም የህመም ስሜቶች

ጥርቅም ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

10

ምንም እንኳን በተለምዶ ኤች አይ ቪን ከኤድስ ጋር

አንድ እና ተመሳሳይ አድርጎ የማየት ሁኔታ ቢኖርም

ኤድስ ቫይረሱ በደም ውስጥ ከተከሰተ በኋላ ቆይቶ

የሚከሰትና በሽታን ወይም ጤናማ ሰው

የሚቋቋማቸውን ህመሞች ያለመቋቋም ችግር ነው።

ሶስተኛው የክስተት ደረጃ የኤች አይ ቪ ማህበራዊ

ውጤቱን የሚያሳይ ነው። ይህም ውጤት በዋናነት

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ባለባቸውና በኤድስ

በተያዙት እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርስ

መገለልና መድልኦ ነው።

መገለልና መድልኦ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሰዎችን

ዝቅ አድርጎ የማየትና በማህበራዊ ህይወት ውስጥ

ዝቅተኛ ተጠቃሚነትና ሚና እንዲኖራቸው የማድረግ

ሁኔታ ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

11

ቀደም ብሎ በአዕምሮ በሽተኞች፣ በአካል ጉዳተኞች፣

ወዘተ. ላይ የሚከሰተው መገለልና መድልኦ ቅርጹን

ቀይሮና በተጽዕኖ ደረጃም አድጎ ከኤች አይ ቪ ጋር

በተያያዘ እየተከሰተ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

12

መልመጃ 1

1. ኤች አይ ቪ ምንድነው?

2. ኤድስ ከኤች አይ ቪ የሚለየው በምንድነው?

3. ሶስቱ ዋና ዋና የኤች አይ ቪ የክስተት ደረጃዎች

ምንድን ናቸው?

4. ኤች አይ ቪን በተመለከተ የሚከሰት መገለልና

መድልኦ ምክንያቱ ምንድነው ትላላችሁ?

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

13

ኤች አይ ቪን መከላከል

ኤች አይ ቪ/ኤድስ ክትባትም ሆነ መድሃኒት

የለውም፡፡ኤች አይ ቪ ኤድስ ካብዛኞቹ በቫይረስ

ምክንያት ከሚመጡ በሽታዎች የሚለየው ባህርይን

በማስተካከልና በብልህነት መከላከል የሚቻል

መሆኑ ነው፡፡

ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል ዋናውና

መሰረታዊው መፍትሄ ከወሲብ ታቅቦ መቆየት

ነው፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ወሲብ

ሳይፈፅሙ በመቆየት ለማግባትና ትዳር

ለመመስረት በሚታስብብት ወቅት ተመርምሮ

ራስን ማወቅና ከትዳር አጋር ጋር ብቻ ወሲብ

መፈፀም ኤች አይ ቪን ለመከላከልም ሆነ

ለአጠቃላይ ጤናማ ህይወት መፍትሄ ነው፡፡

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

14

ከፍቅረኛ ወይም ከትዳር ጓደኛ ጋር በመተማመን

መኖርና ከጓደኛ ውጭ ከማንም ጋር ወሲብ

አለመፈፀም ሁለተኛ አማራጭ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን አማራጮች ማሟላትና

መጠቀም ካልቻልንና ወሲብ ለመፈፀም ከወሰንን

ኮንዶምን መቶ በመቶ መጠቀም አለብን፡፡ኮንዶምን

መቶ በመቶ መጠቀም ማለት በአጠቃቀሙ ላይ

ዝንፈት ሳያሳዩ በትክክልና በአስተማማኝ ሁኔታ

መጠቅም ማለት ነው፡፡

ለወንዶችም ሆነ ለሴቶችም የተዘጋጀ ኮንዶም ያለ

ሲሆን በተለይ የወንዶች ኮንዶም ሰፊ የስርጭትና

የአጠቃቀም መሰረት ያለው በመሆኑ በቀላሉ

መጠቀም ይገባቸዋል፡፡

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

15

ኮንዶምን ደራርቦ ለመጠቀም መሞከር በሁለቱ

ኮንዶሞች መከላከል የመፋተግ ሂደትን

ስለሚፈጥርና ይህም በኮንዶሙ ደህንነት ላይ

የመላላጥና የመበጣጠስ ችግር ስላለው ኮንዶምን

ደራርቦ መጠቀም ፍፁም ተገቢ አይደለም፡፡

በኮንዶሙ ላይ ያለው ቅባት ፍትጊያን

በመካላከልና ቀላልና ለስላሳ ሂደትን በመፍጠር

ቫይረሱን ለመከላከል ስለሚያስችል ጠቃሚነቱን

መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

አንድን ኮንዶም ካንድ ጊዜ በላይ መጠቀም

አይገባም፡፡

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

16

መልመጃ 2

1. ከወሲብ ታቅቦ መቆየት የመጀመሪያው

ተመራጭ የኤች አይ ቪ መከላከያ መንገድ ነው።

እውነት/ሃሰት

2. በአገራችን የሚሸጡ የኮንዶም ዓይነቶችን ዘርዘሩ፡

3. ስለኮንዶም ከጓደኞቻችሁ፤ከቤተሰባችሁ ወይም

ከሌላ ሰው ጋር ተወያይታችሁ ታውቃላችሁ?

4. ስለ ኮንዶም አጠቃቀም ታውቃላችሁ?

5. ስለ ኮንዶም መወያየት ምን ጥቅም አለው

ብላችሁ ታስባላችሁ?

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

17

ህይወትና ባህርይ

የሰው ልጅ ህይወት በሁለት መሪዎች ይሽከረከራል።

አንደኛው ደመ-ነፍስ ሲሆን ይህ እንስሳትን

የሚመራቸው የተፈጥሮ የመቆየት (Survival)

ሚስጥር ሲሆን ሁለተኛው ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠው

የአዕምሮ መሪ ነው።

በሁለቱ መሪዎች የሚመራው ህይወታችን በስሜትና

በህሊና ጎዳናዎች ይሮጣል። የስሜትና የህሊና ጉዟችን

የተመጣጠነ ካልሆነ ህይወታችን ሀሴትና ደስታ

ይርቃታል።

ስሜት ጊዜያዊ ፈንጠዝያ ወዳለበት አቅጣጫ ሁሉ

ሲያቻኩለን በአዕምሯችን ካልታገዘ ነገን ለዛሬ

መስዋዕት የሚሰጥ ይሆናል። በተመሳሳይ መልኩ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

18

አዕምሮ ብቻውን የሚመራው ህይወት ከደስታ የራቀና

ዛሬን ለነገ መስዋዕት የሚያቀርብ ነው።

ነገንም ዛሬንም ያጤነና የተመጣጠነ የህይወት

አቅጣጫ ደስተኛና ጤናማ ህይወትን ይፈጥራል።

እያንዳንዱ የህይወታችን ክፍል በደስታና በኃሴት

የተሞላ እንዲሆን ስሜታችንና ህሊናችን ሊመጣጠኑ

ይገባል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

19

ኤች አይ ቪ እና የወሲብ ባህርይ

ከኤች አይ ቪ መተላለፊያ መንገዶች መካከል ጥንቃቄ

የጎደለው የግብረ-ስጋ ግንኙነት ከ80 በመቶ በላይ

በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። ለዚህም

የወሲብ ደመ-ነፍስ ትልቅ ሚና ይጫወታል። የወሲብ

ደመ-ነፍስ በሰው ልጅ የደመ-ነፍስ የህይወት አቅጣጫ

ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ።

በዚህ ዘመን በእጅጉ እየተስፋፉ የመጡት የፊልምና

የማስታወቂያ ስራዎች የወሲብ ይዘት ያዘሉ

መሆናቸው በወሲብ ባህርይ ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ።

በተለይም ወሲብን ብቻ አልመው የሚወጡት ልቅ

የወሲብ ፊልሞች (የፖርኖግራፊክ ፊልሞች) በወሲብ

ባህርይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

20

የወሲብ ባህርይ በአግባቡና በጥንቃቄ የሚመራ

ካልሆነና ከአዕምሮ ቁጥጥር ውጭ ከሆነ ለጤናማና

ደስተኛ ህይወት እንቅፋት ይሆናል።

ብዙ ሰዎች የወሲብ ስሜት ከአዕምሮ የራቀ ነው

ብለው ያምናሉ። ነገር ግን ወሲብ ምንም እንኳን

ከደመ-ነፍስ የሚመነጭ እንስሳዊ ወይም ተፈጥሯዊ

ሁኔታ ቢሆንም የሰው ልጅ የሚመራው በደመ-ነፍስና

በአዕምሮ ህብር በመሆኑ ምክንያት ወሲብም በአዕምሮ

ቁጥጥር ስር ያለና መነሻውም ከአዕምሯችን ነው።

ህፃናት ለወሲብ የሚነሳሱት በስነ-ህይወታዊ፣

ማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ወዘተ. ዕድገታቸው ለወሲብ

ዝግጁ ሲሆኑ ነው።

ጥንቃቄ የሌለው ወሲብ ለበርካታ ችግሮች ያጋልጣል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

21

ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ ኤች አይ ቪን ጨምሮ

በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች እንዲስፋፉ፣ ሰዎች

ከዓላማ ጋር የሚጋጭ የህይወት ዘይቤ እንዲኖራቸውና

ዓላማቸውን እንዲረሱ፣ያለ ዕቅድ የሚከሰት ወይም

አላስፈላጊ እርግዝና እንዲገጥማቸው፣ ወዘተ. ሊያደርግ

ይችላል።

አላስፈላጊ ወይም ያለ ዕቅድ የተከሰተ እርግዝና

በወሲብ ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ባለማድረግና

የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን ከሚመለከታቸው

ባለሞያዎች ጋር እየተመካከሩ ባለመጠቀም፣ ኮንዶምን

በአግባቡ ባለመጠቀም ወዘተ. ሊመጣ ይችላል።

በተጨማሪም ከሰዎች ቁጥጥር ውጭ በሆነ በአስገድዶ

መደፈርና መሰል ጉዳዮች ሊከሰት ይችላል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

22

ከአላስፈላጊ እርግዝና ጋር በተያያዘ ብዙ ሴቶች

ለጤና አስጊ ወደ ሆነ የፅንስ ማስወረድ እርምጃ

ይገባሉ።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት 54 በመቶ የሚሆኑ

ሴቶች ያለ ዕቅድ የመጣን ፅንስ ለማስወረድ

በህክምና ሙያ ያልሰለጠኑ ሰዎችን/ልማዳዊ የውርጃ

ዘዴን ይከተላሉ።

ይህም በእናቶች ጤንነት ላይ ከሚያሳድረው

የጤንነት ችግር ባሻገር ንፅህናና ጥንቃቄ በጎደላቸው

መሳሪያዎች ምክንያት ኤች አይ ቪ በቀላሉ

እንዲተላለፍ ያደርጋል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

23

መልመጃ 3

ስለ ወሲብ ምንነትና እንዴት ወሲብን መቆጣጠር

እንደሚቻል ከጓደኞቻችሁ ጋር ተወያዩ።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

24

የኤች አይ ቪ መተላለፊያ መንገዶች

ኤች አይ ቪ በሰውነታችን ውስጥ ባሉ ፈሳሾች ሁሉ

ሊገኝ የሚችል ሲሆን ለመተላለፍ በቂ የሆነ ቫይረስ

የሚገኘው በዋናነት በደም ውስጥ፣ በወንድ የብልት

ፈሳሽ ውስጥ ፣ በሴት የብልት ፈሳሽ ውስጥና በጡት

ወተት ውስጥ ነው።

በዚህም ምክንያት ኤች አይ ቪ ጥንቃቄ በጎደለው

የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ስለታማ ነገሮችን አብሮ

በመጠቀም፣ በእናት ጡት ወተት፣ በህክምና ወቅት

በቫይረሱ የተያዘ ደም በመቀበል ሊተላለፍ ይችላል።

ኤች አይ ቪ ከሰው ልጅ ሰውነት ውጭ የመቆየት

አቅም ስለሌለው ከደም ግንኙነት፣ ከብልት ፈሳሽና

ከእናት ጡት ወተት ውጭ የመተላለፍ ሁኔታው

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

25

እጅግ ደካማ ነው። ስለዚህም ጥንቃቄ የጎደለው

ወሲብ፣ ስለታማ ነገሮችን ካለአግባብ በጋራ መጠቀም፣

በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚከሰት የደም መቀላቀል

እና ከእናት ወደ ልጅ በወተት፣ በውልደትና በእርግዝና

ወቅት የመተላለፍ ሁኔታን በጥንቃቄ በመከላከልና

በማስወገድ የኤች አይ ቪን የመተላለፍና የስርጭት

ሁኔታ መግታት ይቻላል።

ኤች አይ ቪ በዋናነት በስስ የቆዳችን ክፍሎች አካባቢ

(Mucus Membrane) የመተላለፍ ዕድሉ ሰፊ ነው።

ይህም የብልት አካባቢንና የአፍ አካባቢን ያጠቃልላል።

በግብረ-ሥጋ ግንኙነት ወቅት ኤች አይ ቪ

የሚተላለፈው በብልት ፈሳሾች ብቻ ሳይሆን በግንኙነቱ

ምክንያትም ሆነ በሌላ ምክንያት በሚከሰት የብልት

መላላጥና መፋተግ የተነሳ የደም መቀላቀል ሊከሰት

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

26

ስለሚችል በመሆኑ በወንድ እና በሴት ብልት

ከሚደረጉ ግብረ ስጋ ግንኙነቶች ባሻገር በፊንጢጣ

ወይም በአፍ አካባቢ በሚደረግ የወሲብ ግንኙነት

ምክንያት ኤች አይ ቪ በእጅጉ ሊተላለፍ ይችላል።

በተለይም በፊንጢጣ የሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት

ለኤች አይ ቪ መተላለፍ እጅግ ምቹ ሲሆን ይህም

ፊንጢጣ እንደሌሎቹ የወሲብ አካላት የመለጠጥ

ባህርይ ስለሌለው በቀላሉ የመሰንጠቅና የመድማት

ባህርይ ስላለው ነው።

ሴቶች ከወንዶች የበለጠ በቫይረሱ የመያዝ ዕድላቸው

የሰፋ ሲሆን ይህም የወንዱ ብልት (ቁላ) ፈሳሽ (ምንም

እንኳን የሴቷ ፈሳሽም ወደ ወንዱ ብልት ቢገባም)

በቀላሉ ወደ ሴቷ ብልት (እምስ) የመግባት ዕድል

ስላለው ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

27

በተጨማሪም የሴቷ ብልት (እምስ) ሰፊ ስስ ቆዳ/ክፍል

ስላለውና የስስነት መጠኑም እጅግ በጣም ከፍተኛ

መሆኑ፣ ሴቶች ከወንዶች ይበልጥ ለሌሎች በወሲብ

የሚተላለፉ በሽታዎች ተጋላጭ በመሆናቸውና ይህም

በብልት አካባቢ ቁስለት በመፍጠር ቫይረሱ በቀላሉ

እንዲተላለፍ ማድረጉ፣ ከስርዓተ-ፆታ ጋር በተያያዘ

በሴቶች ላይ የሚሰነዘር ወሲባዊ ጥቃትና ዝሙት

አዳሪነት ውስጥ እንዲሰማሩ መሆናቸው፣ በሴት

ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ የተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ

ድርጊቶች፣ ማህራዊና ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖዎች፣

የትምህርት ዕጥረት፣ ወዘተ. ሴቶችን ከወንዶች በበለጠ

ለቫይረሱ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።

በወሲብ የሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች ኤች አይ ቪ

በቀላሉ እንዲተላለፍ ምክንያት ይሆናሉ። በበሽታዎቹ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

28

ምክንያት በወሲብ አካላት ላይ የሚፈጠረው የመላላጥና

የመቁሰል ሁኔታ ቫይረሱ በቀላሉ እንዲተላለፍ

ያደርጋል።

በወሲብ ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎች ምንም

እንኳን ሴቶችን የበለጠ ቢያጠቁም በወንዶች ላይም

ይከሰታሉ።

በወሲብ ምክንያት የሚተላለፉት በሽታዎች ሁለት

ዓይነት ናቸው፡

1ኛ. በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰቱ

2ኛ. በቫይረስ ምክንያት የሚከሰቱ

በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰቱት በመድሃኒት ህክምና

መፈወስ የሚችሉ ሲሆን በቫይረስ ምክንያት

የሚከሰቱት ግን በፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች አማካኝነት

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

29

ምልክቶች ቀድመው እንዳይከሰቱ ወይም እንዳይጠነክሩ

ከማድረግ ባለፈ ፈውስ የሚሰጥ መድሃኒት

አልተገኘላቸውም።

አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግና የበሽታዎቹን

ምልክቶች አስቀድመው ሲያውቁ ወይም ሲጠራጠሩ

ወደ ህክምና ባለሞያዎች በመሄድ አስፈላጊውን ሙያዊ

እርዳታ ማድረግ ያስፈልጋል።

በሴቶች ላይ በሽንትና በግብረ-ስጋ ግንኙነት ወቅት

ያልተለመደ የህመም ስሜት መሰማት፣ ያልተለመደ

ከባድ የወር አበባ መፍሰስ፣ በወሲብ አካላት ላይ

የሚከሰት ህመም፣ ወዘተ. ሲያጋጥም ባለሙያ

በማማከር ችግሩን ማወቅ ያስፈልጋል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

30

በወንዶች ላይም በሽንት ወቅት ያልተለመደ የህመም

ስሜትና በወሲብ አካላት ዙሪያ እንግዳ ስሜት/ለውጥ

ከታዬ ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

31

መልመጃ 4

1. ኤች አይ ቪ የሚተላለፍባቸውን ዋና ዋና

መንገዶች ዘርዝሩ፡፡

2. ኤች አይ ቪ በቀላሉ የሚተላለፍባቸው የአካል

ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? ለምን ይመስላችኋል?

3. ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ቫይረሱ በቀላሉ

የሚተላለፍባቸው ለምን ይመስላችኋል?

4. ያልተጠቀሱ የኤች አይ ቪ መተላለፊያ መንገዶች

አሉ ብላችሁ ታስባላችሁ? በዝርዝር አብራሩ።

5. ከኤች አይ ቪ ውጭ ያሉ በወሲብ የሚተላለፉ

በሽታዎች በኤች አይ ቪ የመተላለፍ ዕድል ላይ

ተፅዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

32

ኤች አይ ቪ የማይተላለፍባቸው መንገዶች

ለቫይረሱ በሚሰጥ የተሳሳተ ግምትና የመተላለፊያ

መንገዶቹን ጠንቅቆ ካለማወቅ የተነሳ ብዙ ሰዎች

በዕየለቱ በሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት

ውስጥ በቫይረሱ የመያዝ ስጋት ያድርባቸዋል።

የሚከተሉት ሁኔታዎች ተደጋግመው የሚነሱና ሰዎች

የሚሰጉባቸው ነገር ግን ቫይረሱ ፈጽሞ

ሊተላለፍባቸው የማይችልባቸው መንገዶች ናቸው።

የመመገቢያ ዕቃዎችን በጋራ በመጠቀም ወይም

አብሮ በመመገብ

እጅ በመጨባበጥ፣ በመተቃቀፍ፣ ጉንጭ

ለጉንጭ በመሳሳም

በወባ ትንኝ ንክሻ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

33

ሽንት ቤት በጋራ በመጠቀም ወይም በመቀመጥ

በሽንት፣ በላብ፣ በትንፋሽ፣ በእንባ፣ በምራቅ

ደሙን በእጅ መንካት (እጅ ተቆርጦ ወይም

ተልጦ ደም መቀላቀል እስካልቻለ ድረስ)፤ የኤች አይ

ቪ ቫይረስ በቆዳ ላይ የመሰንጠቅ ወይም የመላጥ

ሁኔታ ከሌለ ወደ ሰውነታችን ሊገባ አይችልም፤

ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን በቀላሉ ለመግባት የሚችለው

በስስ የሰውነታችን ክፍሎች ማለትም በብልት አካባቢና

በአፍ አካባቢ ነው። ነገር ግን በእጆቻችን አካባቢ

የተላጠ ወይም የተሰነጠቀ ነገር አለመኖሩን እርግጠኛ

መሆን አለብን።

በልብስ

በማበጠሪያ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

34

አብሮ በመተኛት

ቫይረሱ ከሰው አካል ወጥቶ ብዙ መቆየት

ስለማይችል ከደም ንክኪ ውጭ በተለያዩ ቁሳቁሶች

አብሮ በመጠቀምና የአካል ንክኪ በማድረግ

ይተላለፋል ብሎ መስጋት በፍፁም አያስፈልግም።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

35

መልመጃ 5

1. ኤች አይ ቪ የማይተላለፍባቸው መንገዶች ምን

ምን ናቸው?

2. በቫይረሱ የተያዘን ሰው ደም በእጅ መንካት

ቫይረሱን የማያስተላልፈው ለምን ይመስላችኋል?

3. ኤች አይ ቪ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ከሰው አካል

ውጭ ሆኖ መቆየት ይችላል (እውነት/ሀሰት)፤

ምክንያታችሁን አብራሩ።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

36

ኤች አይ ቪ እና ማህበራዊ ችግሮች

ኤች አይ ቪ በርካታ ማህበራዊ ጎኖች ያሉት የጤና

ችግር በመሆኑ ከማህበራዊ ችግሮች እንደ አንዱ

ተደርጎ ይቆጠራል።

ከማህበራዊ ችግሮች ውስጥ እጅግ በጣም መሰረታዊና

ማህበራዊ ደህንነትን የሚያናጉት (ማህበራዊ ጠንቆች)

የሚከተሉት ናቸው፡-

ሴተኛ አዳሪነት፣

የአደገኛ እጾችና የአልኮል ጥገኝነት፣

ቦዘኔነት፣

ወጣት ጥፋተኝነት፣

ለምኖ አዳሪነት፣

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

37

የጎዳና ተዳዳሪነት፣

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና

ኤች አይ ቪ/ኤድስ ናቸው።

ማህበራዊ ችግሮች እርስ በርስ የተቆላለፉና አንዱ

የሌላኛው ደጋፊ በመሆን የህብረተሰቡን ኑሮ በእጅጉ

የሚያናጉ በመሆናቸው ምክንያት በተናጠል ለመፍታት

እጅግ አስቸጋሪ ናቸው።

ስለዚህም እያንዳንዱን ማህበራዊ ችግር በመከላከልና

ራሳችንን በመጠበቅ ከኤች አይ ቪ ነፃ የሆነ ጤናማ

ህይወት መኖር እንችላለን።

በአደገኛ ሱሶች መጠመድ ጥንቃቄ ወደጎደለው ወሲብ

ሊመራን ይችላል፤ ይህም በኤች አይ ቪ እንድንያዝና

ጤናማ ህይወት እንዲርቀን ሊያደርግ ይችላል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

38

በተመሳሳይ ሌሎችም ችግሮች በአንድ ወይም በሌላ

መንገድ ወደ ኤች አይ ቪ ስለሚወስዱን ጥንቃቄ

ማድረግና ጓደኞቻችንም ማስተማር ከእኛ የሚጠበቅ

ተግባር ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

39

ኤች አይ ቪ፣ ሥርዓተ-ጾታና ጎጅ ልማዳዊ

ድርጊቶች

ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች በህብረተሰቡ ውስጥ በልማድ

የሚፈጸሙና በአካል፣ በአዕምሮ፣ በስነ-ልቦና፣

በኢኮኖሚ፣ ወዘተ. ህይወታችን ውስጥ ጉዳት

የሚያደርሱ የህብረተሰቡ የወግና የባህል መጥፎ

ገፅታዎች ናቸው።

ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች በዋናነት በሴቶችና በህጻናት

ላይ የሚደርሱ ሲሆኑ በህብረተሰቡ ውስጥ ለረጅም

ጊዜ የቆየው የተሳሳተ ስርዓተ-ፆታ ትልቁ ምክንያት

ተደርጎ ይጠቀሳል።

ስርዓተ-ፆታ ማለት ማህበረሰቡ ለሴትና ወንድ ፆታዎች

የሚሰጠው የወንድነት እና የሴትነት መለያ ባህርይ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

40

ሲሆን ይህም በሰው ልጅ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ

በሂደት የሚፈጠርና የፆታን ማህበራዊና ባህላዊ ገፅታ

የሚያሳይ ነው።

ፆታ ስነ-ህይወታዊ ወይም ተፈጥሯዊ የወንድነት እና

የሴትነት መለያ ባህሪ ነው።

በቅርብ ጊዜ በሳይንሱ ዓለም ፆታን በህክምና የመቀየር

ሁኔታዎች ቢስተዋሉም በዋናነት ጾታ ሊቀየር

የማይችል ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው።

የተሳሳተና ፍትሃዊ ያልሆነ የስርዓተ-ፆታ መኖር

ፆታዊነት ጎልቶ እንዲወጣ ማለትም ለአንዱ ፆታ

የተጋነነ ግምት የመስጠትና ሌላውን የመናቅ ወይም

የማንቋሸሽ ዝንባሌ እንዲኖርና እንዲስፋፋ አድርጓል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

41

ሴቶች በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ

ሂደቶች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በተሳሳተ ስርዓተ-ጾታ

ምክንያት እጅግ የተገደበ ነው። ይህን ተከትሎ ከቅርብ

ጊዜ ወዲህ የሴቶች መብት አቀንቃኞች (Feminists)

የተለያዩ ሀሳቦችን በማራመድ የሴቶችን የፆታ

እኩልነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ስለሆነም የስርዓተ-ፆታው የተሳሳተ መሆን ሴቶች

የጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ዋነኛ ዒላማ እንዲሆኑ

አድርጓል።

ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እጅግ በጣም ዘርፈ ብዙ

ገጽታና ባህርይ ቢኖራቸውም በዋናነት ግን በሳይንሳዊ

መረጃ ላይ ያልተደገፉ ትውፊታዊ ስነ-ስርዓቶች

የሚንጸባረቁባቸው ናቸው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

42

በተለያዩ ቦታዎችና አገራት የተለያዩ ጎጅ ልማዳዊ

ድርጊቶች ቢኖሩም በአገራችን ላይ ጎልተው

የሚስተዋሉ ዋና ዋና ድርጊቶች ግን ከዚህ

የሚከተሉት ናቸው።

የሴት ልጅ «ግርዛት»፡ የሴት ልጅ ግርዛት የሴት

ህጻናትን ብልት በከፊል ወይም በሙሉ የመቁረጥ

ተግባር ሲሆን ይህም ከቦታ ቦታ የተለያየ ዓይነትና

መጠን ይይዛል። የሴት ልጅ «ግርዛት» ባብዛኛው

በሶስት ዓይነት ሊከፈል ይችላል።

አንደኛው፤ ሱና በመባል የሚታወቀው ከወንድ ልጅ

ግርዛት ጋር የሚመሳሰል እና የላይኛውን የብልት

ክፍል (ላቢያ ማጆራ) በከፊል ወይም በሙሉና

የቂንጥርን ጫፍ የመቁረጥ ሁኔታ ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

43

ሁለተኛው፤ ክላይትሮዴክቶሚ የሚባለው ዓይነት

ሲሆን ይህም በብዙ ቦታዎች የተለመደ ነው። ይህ

ድርጊት የብልትን የውስጥ ክፍል (ላቢያ ማይኖራ) እና

ቂንጥርን ሙሉ ለሙሉ የመቁረጥ ሁኔታ ነው።

ሶስተኛውና በአገራችን ውስጥ በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ

የሚፈጸመው ኢንፉቡሌሽን በመባል የሚታወቀው

እጅግ አሰቃቂ ድርጊት ነው። በዚህ ድርጊት ከላይ

የተጠቀሱት ድርጊቶች እንደተጠበቁ ሆነው

በተጨማሪነት የላይኛው የብልት ክፍል ፈፅሞ

የሚወገድበትና የሴቷ ብልት ለሽንት ቀዳዳ ብቻ

በመተው የሚሰፋበት እንዲሁም በኣንዳንድ ቦታዎች

የተለያዩ ባዕድ ቁሶች የሚሰኩበት ሁኔታ ነው።

ሶስተኛውን ዓይነት «ግርዛት» በተመለከተ

ኢትዮጵያዊቷ የአለም ሞዴል ሊያ ከበደ በተወነችበት

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

44

“The Desert Flower” በሚል ፊልም ላይ የችግሩ

ስፋት በሰፊው ይታያል።

የሴት ልጅ «ግርዛት» ስነ-ልቦናዊ፣ አካላዊና ወሲባዊ

ችግሮችን የሚያስከትል ሲሆን ይህም በወደፊቱ የሴቷ

ህይወት ላይ ከባድ ጠባሳ ይፈጥራል።

የድርጊቱ ዋና መንስኤ ወሲብን በአዕምሮ ቁጥጥር ስር

ያልሆነ የደመ-ነፍስ ውጤት ብቻ እንደሆነ አድርጎ

መመልከት ሲሆን ይህም ወሲብን ለመቆጣጠር በሚል

ሃሳብ ለወሲብ ወሳኝ የሆኑትን የአካል ክፍሎች ወደ

መቁረጥ ያመራል።

በድርጊቱ ምክንያት የተቆረጠው ብልት የመለጠጥ

ባህሪውን ስለሚያጣ በወሲብ ወቅት ከባድ ህመምና

ስቃይ ይፈጥራል። ወደፊትም በወሊድ ጊዜ ከፍተኛ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

45

ችግር እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ይህም ጊዜ ተሻጋሪ

ለሆነው የስነ-ልቦና ችግር ያጋልጣል።

በአጠቃላይ ደህንነት ላይ ከሚያደርሰው ሁለንተናዊ

ችግር ባሻገር ብልትን ለመቁረጥ የሚውሉ ስለታማ

መሳሪያዎች በአግባቡና በጥንቃቄ የማይያዙ

በመሆናቸው ኤች አይ ቪን በቀላሉ ያስተላልፋሉ።

ያለዕድሜ ጋብቻ፡ ህፃናት በአግባቡ ለወሲብ

ሳይደርሱና ዝግጁ ሳይሆኑ እንዲያገቡ የሚገደዱበት

ሁኔታ ነው። ይህ ድርጊት ምንም እንኳን በሁለቱም

ጾታዎች ላይ የሚከሰት ቢሆንም በሴቶች ላይ ግን

በብዛትም በተጽዕኖ ደረጃም ጎልቶ ይስተዋላል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

46

በትምህርት፣ በማህበራዊ፣ በአካል ወዘተ. ላይ

ከሚያደርሰው ወሰን የለሽ ጫና ባሻገር በህጻናቱ ስነ-

ልቦና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል።

ህፃናት በአግባቡ የልጅነት ጊዜያቸውን ካላሳለፉ

በልጅነታቸው ማግኘትና ማደበር ያለባቸውን ነገር

በሙሉ እንዲያጡ ይሆናሉ። ልጅነቱን የተነጠቀ ሰው

ምንድነው? ምን ዓይነት ስብዕና ይኖረዋል?

ልጅነት የሰው ልጅ ባህርይ የሚወሰንበት ዋና ዘመን

እንደሆነ የባህርይ ጥናቶች በሰፊው ያብራራሉ።

ወንድ ልጅን ማስቀደም፡ ይህ ከጠቅላላ የስርዓተ-

ፆታ ስርዓቱ ጋር የተቆራኘ ቢሆንም በሴት ህፃናት ላይ

የሚፈጸመው አድልኦና የተሳሳተ ግምት እጅግ መጠነ-

ሰፊ ጉዳት ያስከትላል። በአገራችን በውልደት ጊዜ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

47

እንኳን ለሴት ህፃንና ለወንድ ህጻን የተለያየ የእልልታ

ብዛት በማስቆጠር የሴትን ልጅ ማንነት ዝቅ አድርጎ

የማየት ሁኔታ ይስተዋላል።

ጆን ስቱአርት ሚል የተሰኘ ሊቅ በሴት ልጅ ላይ

የሚደርሰው መድልኦና ጭቆና ሳይንሳዊ መሰረት

የሌለውና በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ተፈጥሮ በሂደት

የጎለበተ ሁነት እንደሆነ ያብራራል።

በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በተፅዕኖም ሆነ

በብዛት በህፃንነት ዘመን ላይ የከፋ ቢሆንም በሁሉም

የዕድገት ዘመን ላይ ችግሩ ይስተዋላል።

የአገሪቱ ህገ-መንግስት አንቀፅ 35 ሴቶችን በተመለከተ

የፆታ እኩልነትንና ከመጥፎ ድርጊቶች የመጠበቅ

መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

48

በአገሪቱ ላይ ያሉት የቤተሰብ ህጎችም በጋብቻ ውስጥ

ሴቶች የወንዶች የበታች እንዳልሆኑና የእኩልነት

መብት እንዳላቸው ያስቀምጣሉ።

የአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግና ሌሎች ህጎችም

አስገድዶ መድፈር፣ ያለ ዕደሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ

‹ግርዛት›ና ተያያዥ የሆኑ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ

ይከለክላል።

ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸውን ሁለንተናዊ

ተሳትፎ ለማጎልበትና ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ

እያንዳንዳችን ለጓደኞቻችን፣ ለቤተሰቦቻችን፣ ወዘተ.

ግንዛቤ ማስጨበጥና ድርጊቱን በመከላከል ሂደቱም

ከህግ አካላት ጋር በመተባበር መስራት ይጠበቅብናል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

49

በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርስን

በደልና ጥቃት በመከላከልና ትክክለኛ ስርዓተ-ፆታ

እንዲኖር በማድረግ በሴቶች ላይ የሚታየውን የኤች

አይ ቪ ተጋላጭነት መግታትና ተያይዞ የሚመጣውን

መገለልና መድልኦም ማቆም የሚቻልበት ሁኔታን

መፍጠር እንችላለን።

ቀጥሎ የቀረበውን ሰንጠረዥ በመመልከት የችግሩን

ስፋትና አሳሳቢነት መረዳት ይቻላል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

50

የህይወት ዘመን የጥቃት/በደል/ተፅዕኖ አይነት

ፅንስ ሴትን መርጦ ማስወረድ

አራስ/ጨቅላ/ ስሜታዊና አካላዊ ጥቃት፣

የምግብና የህክምና አቅርቦት

ማጣት፣ ወዘተ.

ህፃን ‹ግርዛት›፣ ወሲባዊ ጥቃት፣

የምግብና ህክምና አቅርቦት

ማጣት፣ ወዘተ.

ቆንጆ/ልጃገረድ ለፆታዊ ግንኙነት መገደድ፣

ማስፈራሪያና ዛቻ መቀበል፣ ተገዶ

መደፈር፣ በግዳጅ ዝሙት አዳሪ

መሆን፣ ያለፍላጎት ዝውውርና

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

51

የሌሎች ዓላማ ማስፈፀሚያ

መሆን፣ ወዘተ

አዋቂ በፍቅር/ትዳር ጓደኛ የሚሰነዘር

ጥቃት፣ ስነ-ልቦናዊ ጥቃት፣ በስራ

ቦታዎች የሚደርስ የወሲብ ትንኮሳ

ወይም ጥቃት፣ ወዘተ.

አረጋዊ

ከእርጅና ጋር ተያይዞ የሚመጣ

ጥቃት፣ ዘለፋ፣ ወዘተ.

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

52

መልመጃ 6

1. ስርዓተ-ጾታና ጾታ ልዩነታቸው ምንድነው?

2. ዋና ዋናዎቹን ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ጥቀሱ፡፡

3. በአካባቢያችሁ የሚስተዋሉ ጎጅ ልማዳዊ

ድርጊቶችን ዘርዝሩ፡፡

4. የሴት ልጅ ግርዛት ምን ምን ዓይነት ደረጃዎች

ሊኖሩት ይችላል?

5. ኤች አይ ቪና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ምን

ዓይነት ዝምድና እንዳላቸው አብራሩ፡፡

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

53

አደገኛ ዕፆች፣ አልኮልና ኤች አይ ቪ

አደገኛ ዕጾች ለአካላዊም ሆነ ለአዕምሯዊ ጤንነት

መጥፎ ከመሆናቸውም ባሻገር የውሳኔና በጥልቀት

የማሰብ ክህሎታችንን በማዳከም ወደ ልቅ ወሲብ

በመምራት ለኤች አይ ቪና መሰል በሽታዎች

ያጋልጡናል።

በአገራችን እየተለመደ የመጣው ጫት የመቃም ሁኔታ

በሁለንተናዊ ደህንነታችን ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረ

ይገኛል።

ጫት የአዕምሮ መልዕክት አስተላላፊ የሆኑ

ኬሚካሎችን ስራ በማወክ ጤናማ አስተሳሰብ

እንዳይኖረን ያደርጋል። ከዛም ባሻገር ወደ ሲጋራና

አልኮል በማምራት የከፋ ችግር ይፈጥራል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

54

የአልኮል አጠቃቀማችን ሶስት ዓይነት ሊሆን

እንደሚችል ባለሙያዎች ያብራራሉ።

አንደኛው አልኮልን በአግባቡ መጠቀም ሲሆን ይህም

ከጤናማና ማህበራዊ አልኮል አወሳሰድ ያላፈነገጠ

የአልኮል አጠቃቀም ነው።

ሁለተኛው የአልኮል ስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት ሲሆን ይህ

በብዛትም ሆነ በድግግሞሽ መጠን ከማህበረሰቡና

ከጤናማ አልኮል አወሳሰድ ያፈነገጠ ሲሆን ይህም ስነ-

ልቦናዊ ጥገኝነትን በማስከተል ተጠቃሚው

አጠቃቀሙን ለመቆጣጠር የሚቸገርበት ሁኔታን

ሲፈጥር ነው።

ሶስተኛው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት ሲፈጠር

የሚከሰት ነው። ተጠቃሚው ከስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

55

ባሻገር ስነ-ህይወታዊ ሂደቱም ከአልኮል ጋር በመላመድ

ያለ አልኮል በአግባቡና በደህና ሁኔታ መንቀሳቀስ

ሲሳነው የሚፈጠር ሁኔታ ነው።

አልኮል ጠጥቶ መስከር በአስተሳሰብ ሚዛናዊነት ላይ

ጫና በመፍጠር ወደ ደመ-ነፍሳችን እንድናጋድል

ስለሚያደርግ ጥንቃቄ ወደ ጎደለው ወሲብ ያመራናል፤

ይህም ለኤች አይ ቪ በቀላሉ እንድንጋለጥ ያደርገናል።

በመሆኑም የአደገኛ ዕፆችና አልኮል ተገዢነት

ሳይጠነክርና ሳይዳብር ለማስወገድ የሚከተለውን ዘዴ

መጠቀም ይቻላል።

1. ችግርን በአግባቡ መለየት

ለምሳሌ፣ አልኮል መጠጣት

2. ትክክለኛውን አስቸጋሪ ባሕሪ መለየት

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

56

ለምሳሌ፣ ከልክ በላይ መጠጣት፣ ደጋግሞ

መጠጣት

3. የባህሪ መለወጫ ዕቅድ ማዘጋጀት

3.1. ከችግሩ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ማስወገድ

ለምሳሌ፣ የቢራ ጠርሙስ፣ ወደ

ድራፍት ቤት መሄድ

3.2. አማራጭ ጥሩ ባህሪ ማዳበር

ለምሳሌ፣ ማስቲካ ማኘክ፣ ማኪያቶ

መጠጣት፣ መጽሃፍ ማንበብ፣

መንሸራሸር/የእግር እንቅስቃሴ ማድረግ

3.3. አዲሱን ልማድ ማጠናከር

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

57

ለምሳሌ፣ ከሽርሽር መልስ ፊልም ማየት፣

ጓደኞቻቸው በሚበዙበት ወይም የሚወዱት ሰው

ወደሚያዘወትርበት ካፌ መሄድ

3.4. ወደ ነበሩበት ከባቢ/ሁኔታ መመለስ

ለምሳሌ፣ መጠጥ ቤት ገብቶ ወይም አልኮል

እየጠጣ ካለ ሰው ጋር ተቀምጦ ለስላሳ መጠጣት

3.5. ችግሩንና የችግሩን መጠን መመርመርና

ማጥናት

ለምሳሌ፣ በየቀኑ መጠጣት፣ በየሳምንቱ

መጠጣት፣ ሁለት ቢራ መጠጣት፣ አምስት ቢራ

መጠጣት

4. በዕቅዱ ላይ የተቀመጠውን መተግበር

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

58

4.1. ቀስ በቀስ ማሻሻል/ ባህሪን መለወጥ

ለምሳሌ፣ የመጠጡን መጠንና ድግግሞሽ

መቀነስ፡ ከአምስት ቢራ ወደ ሶስት፣ ከሶስት ወደ

ሁለት

4.2. ለውጡን መለካት፤ ሁኔታውን በማጤን

እንደገና ማቀድ ወይም ዕቅድን ማስተካከል፤ እንደገና

መተግበር፤ ማምጣት የሚፈልጉትን ባህሪ በምናብ

መቃኘት

4.3. ለውጡን በማረጋገጥ ሂደቱን ማጠናቀቅ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

59

መልመጃ 7

1. የአልኮል ስነ-ልቦናዊ ጥገኝነት ስንል ምን

ማለታችን ነው?

2. አደገኛ ዕፆችና አልኮል ለኤች አይ ቪ ምክንያት

የሚሆኑት እንዴት ነው?

3. በአካባቢያችሁ የአደገኛ ዕፆችና የአልኮል ተጠቃሚ

የሆኑ ሰዎችን በአዕምሯችሁ ዘርዝሩ፤ ምን ዓይነት

ተመሳሳይ ባህርይ አገኛችሁባቸው?

4. ካሁን በፊት የአደገኛ ሱሶችና የአልኮል ተገዢ

ከነበሩ ባህርይዎትን ለማስተካከል ምን አስበዋል?

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

60

የበጎ ፈቃድ የስነ-ምክር አገልግሎትና

ኤች አይ ቪ ኤድስ

ስነ-ምክር/Counseling/፡ ስነ-ምክር የሰው ልጅ ስነ-

ልቦናዊ ችግር በሳይንሳዊ መንገድ የሚፈታበት ወይም

መፍትሄ የሚፈለግበት ሂደት ነው።

የሰው ልጅ ባህርይ በተለያዩ ምክንያቶች ጤናማነቱን

ሲያጣና ሰዎች ህይወታቸውን በትክክል መምራት

ሲያቅታቸው ደስተኛና ጤናማ ህይወት ለመምራት

ይቸገራሉ። ስነ-ምክር ይህን ችግር በሳይንሳዊ ሂደት

የምንፈታበት ዘዴ ነው።

ስነ-ምክር ከምክር በእጅጉ ይለያል፤ ምክር (Advice)

ሳይንሳዊ ያልሆነ በቤተሰብ፣ በጓደኛ፣ ወይም በሌላ

ቅርብ ሰው የሚሰጥ የቃል ውይይትን መሰረት ያደረገ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

61

ሂደት ሲሆን በእጅጉ አቅጣጫ የሚያመለክትና ሰዎች

በየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለባቸውና ህይወታቸውን

እንዴት መምራት እንዳለባቸው በመካሪው

የሚወሰንበት ሂደት ሲሆን ስነ-ምክር ግን ተመካሪው

ችግሩን በራሱ እንዲፈታ ወደ ትክክለኛ አዕምሯዊ

ሁኔታ የሚመራ ሳይንሳዊ መንገድ ነው።

ስነ-ምክር በትምህርት፣ በእፅና አልኮል ሱስ፣ በሙያ፣

በኤች አይ ቪ፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ በወንጀለኝነት፣

ወዘተ. ዙሪያ አተኩሮ ሊሰጥ ይችላል።

ስነ-ምክር ችግር ከመከሰቱም በፊትም ይሁን ከተከሰተ

በኋላ ሊሰጥ ይችላል።

የኤች አይ ቪ የምክር አገልግሎት በዋናነት ሁለት

ደረጃዎች አሉት።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

62

አንደኛው፤ ከደም ምርመራ በፊት የሚሰጥ የቅድመ-

ምርመራ የምክር አገልግሎት (Pre-test Counseling)

ሲሆን ይህም አንድ ሰው የደም ምርመራ ከማድረጉ

በፊት ለምርመራው ዝግጁ እንዲሆንና ውጤቱን በፀጋ

እንዲቀበል ለማድረግ የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን

ያለዚህ አገልግሎት ወደ ምርመራ መግባት አስፈላጊ

ስላልሆነ ወደ ምርመራ ከመግባታችን በፊት ይህን

የስነ-ምክር አገልግሎት ማግኘታችንን ማረጋገጥ

ያስፈልጋል።

በቅድመ-ምርመራ ስነ-ምክር ወቅት በቂ ስነ-ልቦናዊ

ዝግጁነት አላዳበርንም ተብሎ ከታሰበ ከባለሙያው ጋር

በመነጋገር በሚሰጠን አቅጣጫ መሰረት በሌላ ቀጠሮ

ተገኝተን የምክር አገልግሎቱን መውሰድና ዝግጁ

መሆን ይጠበቅብናል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

63

የስነ-ምክር ባለሙያው ማናቸውንም የሂደቱን

ሚስጥሮችና በሂደቱ የተደረጉ የቃላት ውይይቶችን

ለሌላ አካል አሳልፎ ለመስጠት የሙያ ስነ-ምግባሩ

ስለማይፈቅድለት የባለሙያውን ጥያቄዎች በአግባቡ

መመለስ ያስፈልጋል።

ወሲብ ከፈጸሙ ከሁለት ወይም ሶስት ወራት ያልበለጠ

ጊዜ ከሆነ በምርመራ ሂደቱ ቫይረሱ መኖሩን

ለማረጋገጥ ስለሚያስቸግር (ይህ ጊዜ “Window

Period” ይባላል) ለባለሙያው ጉዳዩን በግልፅ መናገር

ያስፈልጋል።

ሁለተኛው ደረጃ የድህረ-ምርመራ ስነ-ምክር (Post-

test Counseling) ሲሆን የደም ምርመራውን

ተከትሎ የምርመራ ውጤታችን (Sereostatus)

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

64

ምንም ይሁን ምን በተረጋጋ መንፈስ ለመቀበል

እንድንችል የሚያግዘን ሂደት ነው።

የምርመራ ውጤቱ ፖዘቲቭ ከሆነ ቀጣይ ህይወታችንን

በጤናማነት ለማስቀጠል ምን ማድረግ እንደሚገባን

ለመወሰን የሚያስችል ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬንና

ምክንያታዊነትን ያላብሰናል።

የኤች አይ ቪ የምርመራ ውጤታችን ኔጌቲቭ

የሚያመለክት ከሆነም ለወደፊቱ ምን ዓይነት ጥንቃቄ

ማድረግ እንዳለብንና የህይወት ዘይቤያችን ምን መሆን

እንዳለበት ለማቀድ የሚያስችል ልቦና እንድናዳብር

ያደርገናል።

ከምርመራ በኋላ በምንም ዓይነት ሁኔታ የስነ-ምክር

አገልግሎቱን ሳናገኝ መሄድ የለብንም።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

65

በህይወታችን ውስጥ ማናቸውም ችግሮች ሲገጥሙን

(ለሱስ ስንጋለጥ፣ ውሳኔ ለመስጠት ስንቸገር፣ ወዘተ.)

ለስነ-ምክር ባለሙያዎች ማማከር አስፈላጊ ነው።

የኤች አይ ቪ ምርመራ፡ አንድ ሰው ኤች አይ ቪ

በደሙ ውስጥ መኖሩ የሚረጋገጠው በደም ምርመራ

ብቻ ነው።

በተለያዩ የተሳሳቱ አመለካከቶችና አሉባልታዎች

ምክንያት ብዙ ሰዎች ኤች አይ ቪ በደም ውስጥ

ያለበትን ሰው ያለምርመራ በእይታ ወይም መሰል

ግምት ለመለየት ይሞክራሉ።

የኤች አይ ቪ ምርመራ ማካሄድ ጠቀሜታው እጅግ

የጎላ ነው። መመርመር ውጤቱ ፖዘቲቭ ለሆነ ሰው

ቫይረሱ ወደሌላ እንዳይተላለፍ እንዲጠነቀቅ፣ ጤናውን

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

66

ከሚጎዱ ነገሮች ራሱን በመቆጠብ ጤናማ ህይወት

እንዲመራ፣ የድጋፍና እንክብካቤ ተጠቃሚ እንዲሆን፣

ራሱን ከተለያዩ ህመሞች (Opportunistic Infections)

ቀድሞ እንዲከላከል፣ የጸረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት

ተጠቃሚ እንዲሆን፣ ወዘተ. በማድረግ ጤናማ

ህይወት ለመምራት ያስችላል።

የምርመራ ውጤቱ ኔጌቲቭ ለሆነ ሰው ደግሞ የወሲብ

ህይወቱን እንዲፈትሽ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ

እንዲያደርግ፣ ጤናማነቱን በማረጋገጥ ቀጣይ

ለማድረግ እንዲዘጋጅ፣ ወዘተ. በማድረግ ጤናማ

ህይወትን ለማጽናት ያስችላል።

የኤች አይ ቪ ምርመራ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ስራ፣ ወዘተ.

የሚያስፈልገው አይደለም። ማንኛውም ሰው የኤች አይ

ቪ ምርመራ ማካሄድ ይጠበቅበታል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

67

በተለይም ከጋብቻ በፊት፣ ልጅ ለመውለድ ሲታሰብ፣

ወዘተ. ምርመራን እንደ አንድ ቅድመ-ሁኔታ

ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

ህጻናት እንደተወለዱም ሆነ ከተወለዱ በኋላ የኤች

አይ ቪ ምርመራ እንዲያካሂዱ ማድረግ ውጤቱ

ምንም ቢሆን እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።

ህጻናቱ ኤች አይ ቪ በደሙ ውስጥ ካለ ሰው የተወለዱ

ከሆኑና የህጻኑ የምርመራ ውጤት ነጌቲቭ ከሆነ

በጡት ወተት እንዳይተላለፍበት አስፈላጊውን እርምጃ

ለመውሰድ ያስችላል፤ ውጤቱ ፖዘቲቭ ከሆነ ደግሞ

ለህጻኑ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ እና ድጋፍ

ለማድረግ ያስችላል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

68

እናቶች ከእርግዝና በፊት ምርመራ በማድረግ ቫይረሱ

በደሙ ውስጥ ያለበት ህጻን እንዳይወለድ አስፈላጊውን

ሰብዓዊ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። በእርግዝና ወቅት

ተመርምረው ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ የሆኑ እናቶች

በእርግዝና ሂደቱ ውስጥ ቫይረሱ ወደ ፅንሱ

እንዳይተላለፍ የጤና ባለሙያዎችንና

የሚመለከታቸውን አካላት ማነጋገርና አስፈላጊውን

ምክርና እገዛ ማግኘት ያስፈልጋል።

የኤች አይ ቪ ምርመራ በፈቃደኝነት መካሄድ ያለበት

በመሆኑ ማንም ‹ነፍስ ያወቀ› (መወሰን የሚችል) ሰው

ያለፍላጎቱ ወይም ያለ ዕውቅናው እንዲመረመር

ማድረግ ተገቢ አይደለም።

በአገራችን የኤች አይ ቪ ምርመራ እንዲያደርጉ

የሚገደዱ የወታደራዊ አውሮፕላን አብራሪዎች እና

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

69

(በአገሪቱ ህጎች ላይ ባይጠቀስም) ለስራ ወደ ውጭ

አገር የሚሄዱ ሰዎች ብቻ በመሆናቸው ከነዚህ ውጭ

ያለ ግለሰብ ያለ ሙሉ ፈቃዱ የኤች አይ ቪ ምርመራ

እንዲያደርግ መገፋፋት፣ መወትወት፣ ማስገደድ፣ ያለ

ፈቃዱ ምርመራ ማድረግ፣ ወዘተ. ተገቢ አይደለም።

በመሆኑም ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ

የኤች አይ ቪ ምርመራ እንዲያካሂዱና ራሳቸውን

እንዲያውቁ ለማድረግ በኤች አይ ቪ ዙሪያ መረጃ

መለዋወጥ፣ የሚተላለፍባቸውንና

የማይተላለፍባቸውን መንገዶች ለይቶ ማስረዳት፣

መገለልና መድልኦን መግታትና አስፈላጊው የባህሪ

ለውጥ እንዲመጣ ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች

ጋር በመተባበር መስራት ከሁላችንም የሚጠበቅ

ተግባር ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

70

መልመጃ 8

1. የኤች አይ ቪ የስነ-ምክር አገልግሎት ለምን

ይጠቅማል?

2. የኤች አይ ቪ ምርመራ ማድረግ ያለባቸው

የህብረተሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው?

3. የኤች አይ ቪ ምርመራ ለምን ይጠቅማል?

4. እርስዎ ተመርምረዋል? ስንት ጊዜ?

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

71

የስሜት ልዕልና/ማዕምር (Emotional Intelligence)

ከሰው ልጅ አዕምሯዊ ብቃት (IQ) በበለጠ ሁኔታ

ለሰው ልጅ ስኬታማ ህይወት (Self-actualization)

ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው የስሜት ልዕልና (EI)

እንደሆነ ምሁራን ይገልፃሉ።

ጎልማን የተባለ ምሁር የስሜት ልዕልና 80 በመቶ

የሚሆነውን የሰው ልጅ አቅም እንደሚለካ ያብራራል።

ስሜታዊ ልዕልና የሚከተሉትን ክሂሎች ያጠቃልላል፡

1. ራስን ማወቅ (Self-awareness)

2. ስሜትን መቆጣጠር (Handling Emotions)

3. ተነሳሽነት (Motivation)

4. ስለ ሌሎች ማሰብ (Empathy)

5. ማህበራዊ ክህሎት (Social Skills)

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

72

ስለ ሌሎች ማሰብ (Empathy)

ስለሌሎች ማሰብ ማለት ሌሎች ያሉበትን ሁኔታና

የድርጊታቸውን መንስኤ በአግባቡ መረዳትና እነሱን

ሆኖ ጉዳዩን መመልከት ማለት ነው። ስለ ሌሎች

ማሰብ (Empathy) እና ለሌሎች ማሰብ (Sympathy)

የተለያዩ ነገሮች ናቸው።ስለ ሌሎች ማሰብ ማለት

የሰዎችን ችግር እነሱን ወክሎ ወይም ራሱን በምናቡ

እነሱን ሆኖ ማሰብ ሲሆን ለሌሎች ማሰብ ግን

ለሌሎች የሃዘኔታ ወይም የእንክብካቤ ስሜት ማሳየት

ወይም ያሉበትን ችግር ከውጭ ሆኖ (እነሱን ሳይሆኑ)

መረዳት ማለት ነው።

እያንዳንዳችን ሌሎችን እንደጥፋኛ ስንቆጥር፣ እድለ-

ቢስነታቸውን ስንናገር፣ በሌሎች ላይ መጥፎ ሃሳብ

ስናስብ ወይም መጥፎ ድርጊት ስንፈፅም እነሱን ሆነን

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

73

ወይም እነሱ ያሉበት ሁኔታ ውስጥ ራሳችን ብንሆን

ብለን በትክክለኛ ሁኔታ ማሰብ ነው።

ስለሌሎች ማሰብ ሶስት የዕድገት ዓይነቶችን ወይም

ብቃቶችን ይጠይቃል።

አንደኛ፤ በአዕምሮ ማደግ ሲሆን ይህም የምናብ

ችሎታን የሚጠይቅ ነው። በሰዎች ላይ ለመፍረድ

ወይም ስለሰዎች ያለንን አመለካከት ትክክለኝነት

ለማረጋገጥ ራስን በሌሎች ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ

አድርጎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ይህ የአዕምሮ ዕድገት

ወይም ብቃት ነው፡፡

የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመመለስ አዕምሯዊ

ዕድገታችሁን መዝኑ፤

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

74

1.የምትጠሉትን ወይም የምትጠሏትን

የምትናደዱበትን ወይም የምትናደዱባትን አንድ ሰው

አስታውሱ፡፡

2.ለምን እንደምትጠሏት/እንደምትጠሉት አስቡና

ምክንያታችሁን አስቀምጡ፡፡

3. እናንተ ብትሆኑ ምን ታደርጉ ነበር?

4. ከእናንተ ሃሳብ/ድርጊት የሷ/የሱ የሚለየው

በምንድን ነው?

5.ድጋሜ ስለሷ/ሱ አስቡ፡፡

ሁለተኛ፤ የስሜት እድገት ሲሆን ይህም የሌሎችን

ሁኔታና ችግር ያገናዘበ የሃዘኔታ ወይም የርህራሄ

ስሜት ማዳበር ማለት ነው፡፡የሌሎችን ሁኔታ ወይም

ችግር ማወቅ ወይም ማገናዘብ ብቻ ትርጉም ስሌለለው

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

75

ከራሳችን ፍላጎት በመነሳት ልናዝንላቸውና ፍቅር

ልናሳያቸው ይገባል፡፡

ሶስተኛ፤ የማህበራዊ እድገት ሲሆን ከሰዎች ጋር

ያለንን ግንኙነትና ቀረቤታ የሚያመላክት ነው፡፡ስለ

ሰዎች በትክክለኛ መንገድ ለማሰብና ሁኔታዎችን

ተረድቶ ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር ከሰዎች ጋር ያለን

የግንኙነትና የመግባባት ክህሎት የዳበረ መሆን

አለበት፡፡

ስለዚህ ስለ ሌሎች በትክክለኛ መንገድ ለማሰብና ጥሩ

ግንኙነት ለመፍጠር ነገሮችን ባግባቡ ማመዛዘንና

ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ መገንዘብና ማሰላሰል፤ለሰዎች

ሰብዓዊና ወንድማዊ/እህታዊ ስሜትና ክብር ማሳየት

እንዲሁም በግልፅነትና በመደማመጥ መግባባት

ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ስለ ሌሎች ማሰብ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

76

(empathy) የምንለውን ትልቅ የህይወት መርህ

ወይም እሴት ተላበስን ማለት ነው፡፡

በእያንዳንዱ ድርጊታችንና በሰዎች ላይ በምንፈፅመው

ወይም በምናስበው ድርጊት ሁሉ በቅድሚያ ስለ ጉዳዩ

ማንሰላሰል ያስፈልጋል፡፡

ስለ ሌሎች የሚያስብ ሰው በማንም ላይ አያሾፍም፤

ማንንም አይሳደበም፤ያለ አሳማኝ ምክንያት አይርቅም፤

የሰዎችን ችግር የመረዳት የአዕምሮ፤የስሜትና

ማህበራዊ ችሎታ አለው፤ለመተቸት፣ ለማማት ወይም

ለማንሾካሾክ አይቸኩልም።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

77

መልመጃ 9

1. አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ባለባቸው ሰወች

ወይም በቤተሰባቸው ወይም በልጆቻቸው ላይ ሰራን

/አሰብን ያላችሁት መጥፎ ነገር ካለ ለማስታወስ

ሞክሩ፡፡

2. ለምን ያን ስህተት እንደሰራችሁ ምክንያታችሁን

አስታውሱ፡፡

3. አሁን ስለዛ ስህተታችሁ ምን ይሰማችኋል?

4. ከአሁን በኋላ ተመሳሳይ ስህተት ላለመድገም

ምን አሰባችሁ?

5. ወላጆቻቸውን ስላጡና ለችግር ስለተጋለጡ

ህፃናት አስባችሁ ታውቃላችሁ?

6. ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ

ህፃናትን በችግራቸው ዙሪያ ቀርባችሁ

አወያይታችኋቸው ታውቃላችሁ?

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

78

7. ስለሌሎች በማሰብ ዙሪያ ከጓደኞቻችሁ ጋር

ተወያዩ፤ማንኛችሁ የተሻለ ስለሌሎች ማሰብ

እንደምትችሉ ማስረጃ እያቀረባችሁ ተነጋገሩ፤

ለቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ተወያዩ፡፡

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

79

መገለልና መድልኦ

መገልና መድልኦ ኤች አይ ቪ በደም ውስጥ መኖሩን

ወይም በኤድስ መያዝን ተከትሎ ቫይረሱ በደማቸው

ውስጥ ባለባቸው እና በቅርብ ዘመዶቻቸው ላይ

የሚመጣ ዝቅ አድርጎ የማየት ሁኔታ ነው።

ይህ ሁኔታ የሚጀምረው በቂ ያልሆነ ወይም የተሳሳተ

መረጃን ተከትሎ እያደገ በሚመጣ ምክንያት የለሽ

ወይም አሉባልታ-ተኮር አስተሳሰብ (Sterotype) ነው።

ይህ አስተሳሰብ በጊዜና በሌሎች ምክንያቶች እየጠነከረ

ሲሄድ በበቂ መረጃ እንኳን ለመቀየር አስቸጋሪ ወደሆነ

የዋልታ አዝማሚነት አስተሳሰብ (Prejudice)

ይቀየራል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

80

መገለልና መድልኦ ተግባራዊ ጫናዎች ሲሆኑ

የተለያየ ቅርፅና ይዘት ሊኖራቸው ይችላል።

መገለል ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን

እንዲሁም ከነሱ ጋር ቅርበት ያላቸውን ሰዎች

የማራቅ ወይም የመራቅ ተግባር በመፈፀም በተለያዩ

ማህበራዊ ሁነቶች ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚገደዱበት

ወይም የሚዳረጉበት ነው።

መድልኦ ደግሞ ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ

ባለባቸውና ለነሱ ቅርብ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚፈፀም

የእኩል ተጠቃሚነታቸውን የመጋፋትና

ከአገልግሎቶች የመገደብ ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታ ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

81

የመገለልና መድልኦ ዓይነቶች

መገለል እና መድልኦ የሚከተሉትን ዋና ዋና ቅርፆች

ይዞ ሊከሰት ይችላል፡-

1. አካላዊ መገለልና መድልኦ፡- ይህ በአካል

የመራቅ፣ አለመቅረብ፣ ከንክኪ መሸሽ፣ አልጋ

መለየት፣ ወዘተ. የሚያጠቃልል ሲሆን በሰዎቹ

ላይ የሚያሳድረው ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ እጅግ የጎላ

ነው።

ኤች አይ ቪ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች ውጭ

ኤች አይ ቪ ይተላለፋል ብሎ መስጋትና

ስጋትንም በተግባር መግለጽ ከሳይንሳዊ

አስተሳሰብ የራቀ ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

82

ይህ አስተሳሰብ በአንድ በኩል መተላለፊያ

መንገዶቹን በደንብ አጥርቶ ካለማወቅ በሌላ

በኩል ደግሞ በከፊል ህሊና (Sub-concsious)

ምክንያት በሚፈጠር ከምክንያት የራቀ ፍራቻ

የሚመጣ ነው።

2. ማህበራዊ መገለልና መድልኦ፡- ይህ ከማህበራዊ

ተሳትፎ፣ ከማንነትና አካባቢያዊ ሚና የማራቅና

እንደ እንግዳ ደጋግሞ በሰውየው ላይ የማፍጠጥ

ሁኔታ ነው።

በማንኛውም ማህበራዊ ህይወታችን ውስጥ

በእኩልነትና በምክንያታዊነት ላይ ያልተመሰረተና

በፍርሃትና በአሉባልታ የታጠረ ማህበራዊ

ስርዓት ለማንኛችንም የሚጠቅም አይደለም።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

83

3. የቃላት መገለልና መድልኦ፡- ይህ ሁኔታ

በዋናነት ቫይረሱን ከሃጢያትና ከሞራል ህግ

ጥሰት ጋር በማዘመድ የሚመጣ ሲሆን በሰዎቹ

ላይ ማሾፍን፣ መውቀስን፣ ማንሾካሾክን፣

ስድብን፣ ወዘተ. የሚያጠቃልል ነው።

4. ተቋማዊ መገለልና መድልኦ፡- ይህ በተለያዩ

ማህበራዊ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ

ተቋማት በኩል የሚስተዋል ፍትሃዊና ሰብዓዊ

ያልሆነ ድርጊትና እርምጃን የሚያጠቃልል ነው።

ተቋማዊ መገለልና መድልኦ በት/ቤቶች፣ በጤና

ተቋማት፣ በስራ ቦታዎች ወዘተ. ተደጋግሞ

የሚታይ ሲሆን በዋናነት በእኩልነት መብት ላይ

ያነጣጠረና አድሏዊ አሰራርን የሚያመለክት

ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

84

የመገለልና መድልኦ ክስተት የሚነባበርባቸው

ሂደቶችና ሁኔታዎች መኖራቸው ጉዳዩን የበለጠ

አሳሳቢ ያደርገዋል።

ከፆታ፣ ከዕፅና አልኮል ሱሰኝነት፣ ከዝሙት

አዳሪነት፣ ከአካል ጉዳተኝነት፣ ከዘውግ ማንነት

ወዘተ. ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች የድርብርብ

መገለልና መድልኦ ዒላማዎች ይሆናሉ።

ቫይረሱን ከተለያዩ ማንነቶች ጋር በማያያዝ

የማንነት ውጤት አድርጎ መመልከት ሰፊ ስነ-

ልቦናዊ ጉዳትን የሚያስከትል ከመሆኑ ባሻገር

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሌለባቸውም

የማዘናጊያ ደወል ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ነገር ግን

የምርመራ ውጤታቸውን በግልፅ ላላሳወቁ ሰዎች

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

85

ውጤታቸውን እንዲሸሽጉ መልዕክት የሚሰጥና

በዚህም ምክንያት የበሽታውን ስርጭት

ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያዳክም

ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

86

መልመጃ 10

1. መገለል ማለት ምን ማለት ነው?

2. መድልኦ ማለት ምን ማለት ነው?

3. በአካባቢያችሁ ወይም በት/ቤት የታዘባችሁት

መገለልና መድልኦ ካለ አብራሩ፡፡

4. የመገለልና መድልኦ ዓይነቶችን ዘርዝሩ፡፡

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

87

የመገለልና መድልኦ ሂደት

ኤች አይ ቪ ከራስ ቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ሊተላለፍ ይችላል የሚል ስጋት

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚኖሩትን መፈረጅ

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጎ ማየት፤ ማግለል

የተገለሉ ሰዎችን የተለያዩ አገልግሎቶች እንዳያገኙ መከልከል፤ በእኩልነት የመጠቀም መብታቸው ላይ መድልኦ መፈፀም

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

88

መገለል፣ መድልኦ እና ህፃናት

ህፃንነት

በህፃናት መብቶች ኮንቬንሽንና በአገራችን ህግ መሰረት

ህፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች

የሆነ ሰው እንደሆነ ተቀምጧል።

በሰው ልጅ እድገትና የባህርይ ጥናቶች መሰረት ከ1-11

ዓመት ያለው ዕድሜ ባብዛኛው የህፃንነት ጊዜ እንደሆነና

ከ12-18 ዓመት የሚሞላቸው ደግሞ በጉርምስና

(Adolescence) ደረጃ ውስጥ እንደሚጠቃለሉ

ይታመናል። ያም ሆኖ የቆይታ ዕድሜ (Chronological

Age) ብቻ የዕድገት ደረጃን ለመወሰን እንደማያስችል

ምሁራን ያብራራሉ። ትክክለኛ የዕድገት ደረጃ

የሁለንተናዊ ለውጦች ድምርና ህብር ውጤት ነው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

89

ኤች አይ ቪ እና ሕፃናት

በኤች አይ ቪ ምክንያት በርካታ ህጻናት ያለ አሳዳጊና

ተንከባካቢ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ ይገኛሉ።

ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ፣ ወይም የታመሙባቸውና

ለአደጋ የተጋለጡ ህፃናት ከሚደርስባቸው ሁለንተናዊ

ችግር ባሻገር የመገለልና መድልኦው ችግር ተካፋይ

ናቸው።

ህፃናት በአካል፣ በአዕምሮ፣ በስሜት፣ በኢኮኖሚ፣

ወዘተ. ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ያልቻሉ በመሆናቸው

ችግሮችን ለመቋቋም እጅግ ይቸገራሉ።

ስለዚህም እያንዳንዳችን ህፃናቱን ለመታደግና በፍቅርና

በእንክብካቤ ለመጠበቅ ያደረግነውን ግለሰባዊም ሆነ

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

90

ማህበራዊ አስተዋፅኦ መፈተሽና ሀገራዊ ኃላፊነታችንን

በአግባቡ መወጣት ይጠበቅብናል።

በህፃናት ላይ የሚደርስን ማናቸውም ተፅዕኖና ከኤች

አይ ቪ ጋር በተያያዘ የሚደርስባቸውን መገለልና

መድልኦ ለመታገል ህፃናት ራሳቸው ትልቁን ድርሻ

መውሰድ አለባቸው።

ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናት

በት/ቤትና በአካባቢያቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና

ትምህርታቸውንም በአግባቡ እንዲከታተሉ ከመገለልና

መድልኦ የፀዳ በፍቅርና እንክብካቤ የተሞላ ጤናማ

ግንኙነትና ቀረቤታ ልንፈጥርና ፍቅራችንን ልናሳያቸው

ይገባል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

91

በተለይም በጉርምስና ዘመን ውስጥ ሊጠቃለሉ የሚችሉ

ህፃናት እርስ በእርሳቸው እንዲማማሩና እንዲተራረሙ

ያስፈልጋል።

የተለያዩ ክበባትን በማዋቀር፣ የህፃናት ፓርላማን

በማጠናከር፣ የውይይት አጀንዳዎችን በማዘጋጀትና

በመወያየት የጋራ የሆነ መብታቸውን በእኩልነትና

በመተባበር መንፈስ ማስከበር ያስፈልጋል።

እርስ በእርስ በሚፈጠር ማህበራዊ ግንኙነትም ስህተት

የሰራውን ሰው ለይቶ የማረምና የመማማር ባህል

ማዳበር ያስፈልጋል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

92

በአጠቃላይ ህፃናቱ እንዳይገለሉና መድልኦ

እንዳይፈፀምባቸው ብሎም በሁለንተናዊ ተሳትፏቸው

ንቁ እንዲሆኑ እያንዳንዳችን የበኩላችንን ኃላፊነት

መወጣት ይገባናል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

93

የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀፅ 2

1. የኮንቬንሽኑ አባል አገሮች በግዛታቸው ክልል የሚገኝ እያንዳንዱ

ህፃን በራሱ ወይም በወላጆቹ ወይም በአሳዳጊው ዘር፣ ቀለም፣

ፆታ፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት፣ የፖለቲካ ወይም ሌላ አስተሳሰብ፣

ዜግነት፣ ነገድ፣ ወይም የትውልድ ስፍራ፣ ሀብት፣ የአካልና

የአዕምሮ ጉድለት፣ ትውልድ ወይም ሌላ የማህበራዊ ኑሮ ደረጃ

ምክንያት ምንም ዓይነት መድልኦ ሳይደረግበት የመብቱ

ተጠቃሚ እንዲሆን በኮንቬንሽኑ የተረጋገጡትን መብቶች

ያከብራሉ፤ ተግባራዊነታቸውንም ያረጋግጣሉ

2. የኮንቬንሽኑ አባል አገሮች ህፃኑ በወላጆቹ በአሳዳጊዎቹ፣ ወይም

በቤተሰቦቹ የማህበራዊ ኑሮ ደረጃ፣ ተግባሮች፣ አመለካከት፣

ወይም እምነት ምክንያት መድልኦ እንዳይደረግበትና አላግባብ

ቅጣት እንዳይደርስበት ለማረጋገጥ ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን

ይወስዳሉ።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

94

መልመጃ 11

1. በህፃናት መብቶች ኮንቬንሽንና በአገራችን ህግ

መሰረት ህፃን ማለት ምን ማለት ነው?

2. ጉርምስና ምንድነው?

3. ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ በህፃናት ላይ

የሚደርሰውን መገለልና መድልኦ ለማስቆም

ከመምህራን፣ ከወላጆችና ከተማሪዎች ምን

ይጠበቃል?

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

95

የመገለልና መድልኦ ውጤቶች

መገለልና መድልኦ ሰፊና አስከፊ ውጤቶች

የሚያስከትል ሲሆን ኤች አይ ቪን ለመከላከል

በሚደረገው ጥረት እጅግ ትልቅ መሰናክል ነው።

በመገለል ተፅዕኖ ላይ ትኩረት እስካላደረግን ድረስ

የምናደርገው ጥረት ሁሉ ስኬት ሊኖረው አይችልም።

በታሪካችን ከተከሰቱት በሽታዎች ሁሉ ከመገለል ጋር

በመቆራኘት አንደኛው ኤድስ ሳይሆን አይቀርም።

-ኤድዊን ካሜሮን

ኤች አይ ቪ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለመከላከል

በሚደረገው ጥረት ውስጥ መገለል፣ መድልኦ እና

የተዛባ ስርዓተ-ፆታ ዋናዎቹ መሰናክሎች ናቸው።

-ፒተር ፓዮት

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

96

መገለልና መድልኦ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው

ሰዎች ለመከላከል ሂደቱ የሚጫወቱትን ሚና

በማመናመን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት

የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፈ ይገኛል።

የኤች አይ ቪ ምርመራን ተከትሎ የሚመጣን መገለልና

መድልኦ በመፍራት ብዙ ሰዎች የበጎ ፈቃድ የምርመራ

አገልግሎት እንዳያገኙ ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ

ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ያወቁ

ሰዎች በመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች

ግለሰቦችና ማህበረሰብ አቀፍ-ተቋማት (ዕድሮች፣

ጀምያዎች፣ ወዘተ.) የሚሰጠውን የህክምናና ሌሎች

ድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎቶች እንዳይጠቀሙ እያደረገ

ይገኛል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

97

ህፃናት በመገለልና መድልኦ እጅግ ከሚጎዱ የማህበረሰብ

ክፍሎች ዋነኞቹ ሲሆኑ በአዕምሮ፣ በስነ-ልቦናና

በማህበራዊ ክሂላቸው ውሱንነት ምክንያትም ተፅዕኖው

የጎላ ይሆናል።

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለ እና ወላጆቻቸውን ያጡ/

በህመም ምክንያት ከወላጆቻቸው አስፈላጊውን

እንክብካቤ ማግኘት ያልቻሉ/ ህፃናት በራሳቸውም ሆነ

በቤተሰባቸው ላይ በሚደርሰው መገለልና መድልኦ

ምክንያት ለሰፊ ስነ-ልቦናዊ ጉዳት እየተዳረጉ ይገኛሉ።

በአገራችን የሚገኙ ከአስራ አምስት በላይ የሚሆኑ

ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ዓይነት

(ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ

ህፃናት፣ በዝሙት አዳሪነት የተሰማሩ ህፃናት፣ ወዘተ.)

እንዲበራከቱና የችግሩ መጠን በስፋትም በጥልቀትም

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

98

እንዲጨምር ኤች አይ ቪ ትልቅ ምክንያት ሆኗል።

በመሆኑም በዚህ የችግሩ ልኬት መሰረት ከኤች አይ ቪ

ጋር በተያያዘ የሚፈፀመው መገለልና መድልኦ

መንሰራፋቱ እያንዳንዳችን በጥልቅ ልናስብበት የሚገባን

አንገብጋቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለክታል።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

99

መልመጃ 12

1. መገለልና መድልኦ ምን ውጤት ያስከትላል?

2. በመገለልና መድልኦ ምክንያት ትምህርት

ያቋረጡ፣ ብቸኝነት የሚያበዙ፣ የሚተክዙ

ህፃናት አይታችሁ ተውቃላችሁ?

3. መገለልና መድልኦን መግታት ኤች አይ ቪን

ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ምን

አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?

4. በመገለልና መድልኦ ዙሪያ ከአሁን በፊት

የተማራችሁት፣ ያነበባችሁት ወይም በሚዲያ

ያዳመጣችሁት ነገር ካለ በማስታዎሻ

ደብተራችሁ በማስፈር ከጓደኞቻችሁ ጋር

ተወያዩባቸው።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

100

5. በአካባቢያችሁ፣ በት/ቤት ወይም በሌላ ቦታ

የታዘባችሁትን እያነሳችሁ መገለልና መድልኦን

እንዴት መግታት እንዳለባችሁ ተወያዩ።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

101

ስለ ኪቱ ያላችሁን አስተያየት፡

በስልክ ቁ. 0918-74-35-85

በኢሜል አድራሻ dareconsultant@gmail.com

ፖ.ሳ.ቁ 970

ወይም

በስልክ ቁ. O58-220-58-89

በኢሜል አድራሻ ossabd@ethionet.et

ፖ.ሳ.ቁ 877

አድርሱን።

የባህርይ ለውጥ መግባቢያ ኪት

102